አዲስ አበባ፡- “አገር የግል እና የተወሰኑ ቡድኖች መጠቀሚያ አይደለችም። ስለዚህ ሁሉም በጋራ የኢትዮጵያን አንድነት ሊጠብቅ ይገባል” ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም ጥሪ አቀረቡ፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ትናንት በፍሬንድ ሺፕ ሆቴል ባዘጋጀው የህዝብ ለህዝብ መድረክ ላይ አፈጉባኤዋ ወይዘሮ ኬሪያ እንደተናገሩት፤ በግለሰቦች እና በተወሰኑ ቡድኖች ምክንያት በተለይ ባለፉት ሁለት እና ሦስት ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች በየክልላቸው በሰላም ወጥተው መመለስ እየተቸገሩ ነው፡፡በብሄራቸው እና በሃይማኖታቸው ምክንያት በህይወታቸው እና በንብረታቸው ላይ ግፍና በደል እየደረሰባቸው ነው። የመንግሥት፣ የህዝብ እና የሃይማኖት ተቋማት ንብረት ሃይ ባይ በሌለበት እየወደመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
‹‹ለአስከፊው አደጋ የተጋለጥንበትን ውጫዊና ውስጣዊ ምክንያት መጥቀስ ቢቻልም ከምንም በላይ የሁላችንም ድርሻ አለበት›› ያሉት አፈ ጉባኤዋ፤ በስምምነትና በዘላቂነት ችግሮችን ለመፍታት ከተሰራ የማይፈታ ችግር አይኖርም ብለዋል፡፡ ለዚህም በችግሮቹና በመፍትሄዎቹ ላይ ውይይት ያስፈልጋል በማለት ገልፀዋል፡፡ የህዝብ ለህዝብ መድረኩ ለመዘጋጀቱ ዋነኛው ምክንያት ይሄ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ አፈጉባኤዋ ገለፃ፤ ህዝቦች ከተጋረጠባቸው አደጋ እንዲወጡ እንዲሁም ሰላምና ደህንነታቸውን ለመጠበቅ የህግ የበላይነትን በማስከበር የዜጎችን ህገ መንግስታዊ መብት እንዲከበር ሁሉም በአንድነት ሊቆም ይገባል፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክብረ በዓልን በማስመልከት የተዘጋጀው የምዕራብ ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች የህዝብ ለህዝብ የጋራ የምክክር መድረክ እንዲሳካ ሁሉም የድርሻቸውን በመወጣታቸው ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል፡፡
‹‹ህገ መንግሥታዊ ቃልኪዳናችን ለዘላቂ ሰላም›› በሚል በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት አዘጋጅነት ዘንድሮ ለ14ኛ ጊዜ የሚከበረውን የኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች በዓል ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው የህዝብ ለህዝብ መድረክ ላይ የኦሮሚያ፣ አማራ፣ ጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል።በወቅታዊ ጉዳዮች እና በጋራ እሴቶች ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው የየክልሎቹ ተወካዮች ምክክር አድርገውበታል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 7/2012
ዳግም ከበደ