አዲስ አበባ፡- በኦሮሚያ ክልል ለሚገኙ አካባቢዎች የእንስሳት፣ ተፈጥሮ ሃብት እና የግብርና ምርት እድገት የሚረዱ 147 የተለያዩ አይነት ቴክኖሎጂዎችን ማቅረቡን የኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
በኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የግብርና እድገት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ዳኛቸው ሉሌ እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱ ባቋቋማቸው 17 ማዕከላት ከዓለም ባንክ በኩል በቀረበው የግብርና እድገት ፕሮጀክት አማካኝነት በርካታ የግብርና ማሻሻያ ቴክኖሎጂዎች ቀርበዋል ። በዚህም ኢንስቲትዩቱ በአጠቃላይ 147 የምርት መሰብሰቢያ፣ እንስሳት መርቢያ እና ለተለያዩ የተፈጥሮ ሃብት የሚያገለግሉ የተሻሻሉ መሳሪያዎችን ከማምረት ጀምሮ ከውጭ አምጥቶ እስከ ማላመድ የደረሰ ስራ አከናውኗል።
እንደ አቶ ዳኛቸው ገለጻ፤ በኢንስቲትዩቱ ስር በሚገኙ አራት ማዕከላት በተለይ የኢንጂነሪንግ ወርክሾፕ ተቋቁሞ በየጊዜው የተሻሻሉ የግብርና ምርት ማሳደጊያ መሳሪያዎችን በመስራት ወደ አርሶአደሩ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ ይገኛል። ከግብርና ዘርፍ በቡና ምርት ማሻሻያ ላይ ያተኮሩ ቴክኖሎጂዎች በቡድን ለተደራጁ አርሶአደሮች ቀርበዋል። ለአብነት አንድ አነስተኛ የሰብል ማጨጃ ማሽን ወይም የዶሮ መኖ ማቀነባበሪያ ማሽን ሲቀርብ አርሶአደሩ ለ15 እና 16 በቡድን እንዲደራጅ ይደረጋል። በዚህ አይነት የቴክኖሎጂ ሽግግር ከ341 በላይ የአርሶአደሮች ማህበራት ተቋቁመዋል። በቀጣይም ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ድጋፍ ሰጪ ተቋማት ጋር በሚገኝ የገንዘብ እርዳታ ለአርሶአደሩ የሚረዱ የተለያዩ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን ለማቅረብ እየሰራ ይገኛል።
በኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የአሰላ ግብርና ምህንድስና እና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አቶ አያሌው በቀለ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ለኢትዮጵያውያን አርሶአደሮች በሚሆን መልክ የተሻሻሉ የግብርና መሳሪያዎች ከተሰሩ በኋላ አዋጭነታቸው ተጠንቶ ወደ አርሶአደሩ እንዲተላለፉ ይደረጋል። ከዚህ ባለፈ ከውጭ አገራት የመጡ ቴክኖሎጂዎችን የማስተዋወቅና የማላመድ ስራ ይከናወናል ። በዚህ ረገድ በአሰላው ማዕከል ብቻ የጤፍ መውቂያ እና ማጨጃን ጨምሮ 11 ዓይነት የተሻሻሉ መሳሪያዎች ተሰርተዋል።
እንደ አቶ አያሌው ገለጻ፤ በማዕከሉ የሚሰሩ ቴክኖሎጂዎች በነጻ ለአርሶአደሩ የሚቀርቡ ናቸው። በዚህ ረገድ የዶሮ ማቀነባበሪያ ማሽን ተሰርቶ የተሰጣቸው በቡድን የተደራጁ አርሶአደሮች ከእራሳቸው አልፈው መጠነኛ ገቢ በመፍጠር እየሰሩ ይገኛል። የተሻሻሉ መሳሪያዎቹ ምርትና ምርታማነትን ከመጨመር ባለፈ ጊዜና ጉልበትን ይቀንሳል። ለምሳሌ ከበሬ ጋር ተቀናጅቶ በመስመር የሚዘራው ማሽን በአንድ ጊዜ እስከ ሁለት ሄክታር የመዝራት አቅም አለው። ይህ ውጤት ሲታይ የአርሶአደሩን ድካም በመቀነስ ጉልበቱን ለተጨማሪ ስራዎች እንዲውል በማድረግ የግብርና ስራው ላይ ተጨማሪ አቅም መፍጠር ያስችላል።
አዲስ ዘመን ህዳር 7/2012
ጌትነት ተስፋማርያም