ሀዋሳ፡- ህዳር 10 ለሚካሄደው የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ የመራጮች ምዝገባ ያለ እንከን እየተከናወነ መሆኑን የምርጫ አስፈጻሚዎችና የህዝብ ታዛቢዎች ተናገሩ፡፡
በሀዋሳ ከተማ በመነሃሪያ ክፍለ ከተማ የሰላም መንደር ምርጫ ጣቢያ ምርጫ አስፈጻሚ ወይዘሪት ሶስና አበበ እንደተናገሩት፤ ከጥቅምት 26 እስከ ህዳር 5 በምርጫ ጣቢያው አንድ ሺህ 247 መራጮች ካርድ ወስደዋል፡፡ እስካሁን የነበረው የመራጮች ምዝገባ ሂደት አንዳች ችግር የሌለበትና እጅግ ሰላማዊ ነው ብለዋል፡፡
አንዳንድ መታውቂያ ሳይዙ የሚመጡ ነዋሪዎችም የምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የመስሪያ ቤት፣ የትምህርት ቤት መታወቂያዎችን በመጠቀም እንዲሁም ሦስት ምስክሮችን በማቅረብ እንዲመዘገቡ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የጣቢያው የህዝብ ታዛቢ አቶ አሸናፊ ደበሰ በበኩላቸው፤ ካርድ ለመውሰድ የሚመጡ ነዋሪዎች ያለ መዘግየት ተስተናግደው እንዲሄድ እየተደረገ መሆኑን መታዘባቸውን ተናግረዋል፡፡ በስህተት ያለ ቀጣናቸው ለመመዝገብ የሚመጡ ነዋሪዎችም በቀጣናቸው ሄደው እንዲመዘገቡ እየተደረገ ነው፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች የብሄር ማንነትና የፖለቲካ አቋም ሳይለይ፤ በእኩል ዓይን እየታዩ የመራጭነት ካርድ እንዲወስዱ እየተደረገ ነው፤ ይህም ህዝቡ ያለ አንዳች ጫና ይጠቅመኛል ያለውን እንዲመርጥ እንደሚያስችለው አብራርተዋል፡፡ ከ1997 ምርጫ ጀምሮ ሀገራዊና አካባቢያዊ ምርጫዎችን የመታዘብ ልምድ እንዳላቸው የተናገሩት አቶ አሸናፊ፤ በአሁኑ ህዝበ ውሳኔ ለመሳተፍ ህዝቡ እያሳየ ያለው የነቃ ተሳትፎ እጅግ የሚያስደስት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ሀረር ቀበሌ አረጋዊያንና እርሻ ጣቢያ ህብረተሰብ ተሳትፎ ጽህፈት ቤት ምርጫ ጣቢያ ቁጥር 4 የጣቢያው አስተባባሪ ወይዘሮ ተረፈች ታፈሰ በበኩላቸው፤ ባለፉት ዘጠኝ ቀናት 997 መራጮች ካርድ መውሰዳቸውን አንስተዋል፡፡ የመራጮች የምዝገባ ሂደትም ያለ አንዳች ችግር መከናወኑን ተናግረዋል፡፡
የህዝብ ታዛቢ ወይዘሮ ብዙነሽ ጃቤ በተመሳሳይ ምዝገባው ያለ ችግር ሲካሄድ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ በመጀመሪያ ቀናት ያልታደሱ መታወቂያዎችና መሰል ችግሮች ሲያጋጥሙ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ችግሩ ተቀርፏል፡፡ በፓስፖርት እና በምስክር እንዲመዘገቡ በማድረግ ችግሩ እንዲቀረፍ መደረጉን አንስተዋል፡፡
ህብረተሰቡ የወሰደውን ካርድ በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋል አለበት ያሉት ወይዘሮ ብዙነሽ፤ ህዝቡ ካርድ በመውሰድ ረገድ ያሳየውን የነቃ ተሳትፎ በካርዱ የፈለገውን በመምረጥም እንዲደግመው ጠይቀዋል፡፡ ህዳር 10 ለሚካሄደው የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ በ1 ሺ 692 የምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች ምዝገባ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 7/2012
መላኩ ኤሮሴ