የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የወርቅ ደረጃ ከሰጣቸው ታላላቅ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድሮች አንዱ የሆነው የፎኮካ ማራቶን ከሳምንት በኋላ በጃፓን ይካሄዳል፡፡ በዚህ ውድድር የሚፎካከሩ የዓለማችን ጠንካራ አትሌቶች ስም ከወዲሁ ይፋ እየተደረገ የሚገኝ ሲሆን፤ የርቀቱ ኮከቦች የሆኑት ምሥራቅ አፍሪካውያን አትሌቶች የተለመደ የአሸናፊነት ግምት ተችሯቸዋል፡፡
እኤአ በ2015 የቤጂንግ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በማራቶን ተከታትለው በመግባት የወርቅና የብር ሜዳሊያ ማጥለቅ የቻሉት ኤርትራዊው ግርማይ ገብረሥላሴና ኢትዮጵያዊው የማነ ፀጋዬ ትልቅ የአሸናፊነት ግምት ከተሰጣቸው አትሌቶች ግንባር ቀደም ናቸው፡፡
ግርማይ ገብረሥላሴ በዓለም ቻምፒዮናው በአስራ ስምንት ዓመቱ ሳይጠበቅ ለታላቅ ድል በመብቃት ለኤርትራ በመድረኩ የመጀመሪያ የወርቅ ሜዳሊያ ማጥለቁ የሚታወስ ሲሆን፤ በአንፃሩ በርቀቱ የተሻለ ልምድ የነበረው የማነ የብር ሜዳሊውን ለኢትዮጵያ ማስመዝገቡ አይዘነጋም፡፡ ሁለቱ የማራቶን ፈርጦች ከዓለም ቻምፒዮናው በኋላ በትልቅ ውድድር ዳግም ፎኮካ ማራቶን ላይ የሚያደርጉት ፉክክር የሚጠበቅ ይሆናል፡፡
የማነ በበርካታ የማራቶን ውድድሮች በማሸነፍ ስማቸው ከሚጠቀስ የዓለማችን ድንቅ የማራቶን አትሌቶች አንዱ ሲሆን፤ ከሁለት ዓመት በፊት በዚሁ በፎኮካ ማራቶን 2:08:48 ሰዓት ማሸነፉ ይታወሳል፡፡ ይህም ሰዓቱ እኤአ 2012 ላይ በሮተርዳም ማራቶን ሲያሸንፍ ካስመዘገበው የራሱ ምርጥ ሰዓት በአራት ደቂቃ የተሻለ ሆኖ ተመዝግቦለታል፡፡ የማነ በዓለም ቻምፒዮናው የብር ሜዳሊያውን ካጠለቀ ወዲህ ጉልበቱ ላይ በገጠመው ጉዳት የ2016 ሪዮ ኦሊምፒክን ጨምሮ በርካታ ውድድሮች ያመለጡት ሲሆን፤ ያለፈውንም ዓመት በጥሩ አቋም ላይ አልነበረም፡፡ ይሁን እንጂ በ2018 ወደ ጥሩ አቋም መመለሱን ባለፈው ሰኔ ወር የኦታዋ ማራቶንን 2:08:52 በሆነ ሰዓት በማሸነፍ አሳይቷል፡፡
ግርማይ ገብረሥላሴ በበኩሉ ከዓለም ቻምፒዮናው ድሉ በኋላ በሪዮ ኦሊምፒክ ሌላ ታሪክ ይሠራል ተብሎ ሲጠበቅ ሜዳሊያ ውስጥ መግባት ሳይችል ቀርቷል፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ታላቅ መድረክ አራተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ እንደ ወጣት አትሌት መጥፎ የሚባል አልነበረም፡፡
ከኦሊምፒኩ ስድስት ሳምንታት በኋላ በጠንካራው የኒውዮርክ ማራቶን ዳግም ሳይጠበቅ ለድል የበቃው ግርማይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ስሙን በርቀቱ ማግነን ችላል፡፡ 2:07:46 የሆነ የራሱ ምርጥ ሰዓት ያለው ግርማይ ባለፉት ሁለት ውድድሮቹ አቋርጦ መውጣቱ ምናልባትም ወደ ጥሩ አቋሙ ካልተመለሰ በዘንድሮው የፎኮካ ማራቶን ከየማነ ጋር የሚጠበቀውን ጠንካራ ፉክክር እንዳያሳይ ስጋት ሊሆን ይችላል፡፡
በዚህ ውድድር የማነ ከግርማይ ባሻገር ከሌላ አትሌት ጠንካራ ፉክክር እንደሚገ ጥመው ይጠበቃል፡፡ ይህም ውድድሩ ላይ ከየማነ ቀጥሎ ሁለተኛውን ፈጣን ሰዓት ይዞ የሚወዳደረው ኬንያዊው ቪንሰንት ኪፕሩቶ ሲሆን፤ በርቀቱ 2:05:13 የሆነ የራሱ ምርጥ ሰዓት ያለው አትሌት ነው፡፡
በሌላ በኩል በዘንድሮው የፎኮካ ማራቶን ትኩረት ሳይሰጠው መታለፍ የሌለበት አትሌት ጃፓናዊው ዩኪ ካዉቺ ነው፡፡ ይህ አትሌት ካለፉት ዘጠኝ የፎኮካ ማራቶን ውድድሮች በስምንቱ ላይ በመሳተፍ ከሌሎቹ አትሌቶች የተሻለ ልምድ ማካበት ችሏል፡፡ ዩኪ ልምድ ማካበቱ ብቻ በውድድሩ አስፈሪ ወይንም ጠንካራ ተፎካካሪ ባያደርገውም በርቀቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያስመዘገበ ያለው ውጤትና ጥሩ አቀም ለምሥራቅ አፍሪካውያኑ አትሌቶች አስፈሪ ያደርገዋል፡፡ ዩኪ በዚህ ውድድር እኤአ በ2011፣2013እና 2016 ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ በሦስቱም ውድድሮች ርቀቱን ከ2፡10 ሰዓት በታች በማጠናቀቅ ጥንካሬውን ማሳየት ችላል፡፡ ዩኪ ምሥራቅ አፍሪካውያን ደጋግመው ያሸነፉትን የቦስተን ማራቶን በቅርቡ ማሸነፉም በአገሩና በደጋፊዎቹ ፊት በሚያደርገው ውድድር ቀላል ግምት እንዳይሰጠው ያደርጋል፡፡