– በአዴፓ እና በኦዴፓ ሥራ አስፈፃሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ ደረጃ ውይይት ተደርጓል
አዲስ አበባ፡- በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ አሳታፊ ፖለቲካ እየተካሄደ ስለሆነና ሰላም የጋራ አጀንዳ በመሆኑ በስልጣን ላይ ያሉትን ጨምሮ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ያሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በህዝቦች መካከል ቅራኔ ሳይፈጠር አብሮ መኖርና መዝለቅ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መግባባት አስፈላጊ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ገለጹ። በአዴፓ እና በኦዴፓ ስራ አስፈፃሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ ደረጃም ውይይት ተደርጓል።
በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች በሁለቱ ክልሎች ውስጥ የተከሰተውን ችግር አስመልክቶ ትላንት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ ቤት ውይይት አካሂደዋል። በውይይቱ መግቢያ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ እንደተናገሩት፤ በክልሎቹ ውስጥ ፖለቲካዊና ታሪካዊ ቅራኔዎች ካሉ የሰው ህይወት ሳያጠፉ እና ንብረት ሳይወድም በንግግር ሊፈቱ ይገባል።
“በሁለቱ ክልል ህዝቦች ውስጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእነርሱ ወይም በሌሎች ሃይሎች ምክንያት መቃቃር፤ ጠብ፤ ግጭትና የሰው ህይወት መጥፋት እየተባባሰ መጥቷል፤” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግሩን ለመቅረፍ በመንግስት ደረጃ ክልሎችን እየመሩ ያሉ ፓርቲዎች ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
“በኢትዮጵያ ውስጥ የጨዋታ ህጉ በሚጫወቱትም ሆነ በተመልካቾች በደንብ የታወቀ አይደለም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚህ ምክንያት የሚፈጠሩ አደጋዎች የሰው ህይወት የሚያጠፉ፤ ንብረት የሚያወድሙና በዋዛ ፈዛዛ የሚታለፉ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸዋል። “አንደኛው የሌላኛውን ቁስል በትክክል ያለመገንዘብ ችግር እየተስተዋለ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “በጋራ አጀንዳዎች ላይ መነጋገር ለህዝቦች አንድነትና ትስስር ይበልጥ ጠቃሚ ነውም” ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሀላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ውይይቱን አስመልክተው እንደተናገሩት፤ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በተፈጠሩ ችግሮች ዙሪያ በአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /አዴፓ/ እና በኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ/ኦዴፓ/ በስራ አስፈፃሚና በማእከላዊ ኮሚቴ ደረጃ ውይይት ተደርጓል። በውይይት መድረኩ የክልሎቹን ወቅታዊ ሁኔታ በመገምገም ከዚህ የከፋ ጉዳት ሳይደርስ ለማስቆም የሚያስችሉ የመፍትሄ ሀሳቦች መቀመጣቸውንም አቶ ንጉሱ ገልፀዋል።
ችግሩን ለመፍታት ከፓርቲዎቹ ውይይት በተጨማሪ በሀይማኖት አባቶች፤ በሀገር ሽማግሌዎች እና በሁለቱ ክልል ባለሀብቶች መካከል ውይይት መደረጉንና ይህም እንደሚቀጥል የተናገሩት አቶ ንጉሱ፤ ዛሬ ደግሞ በሁለቱ ክልል ምሁራን መካከል ውይይት እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ፓርቲዎቹ በኢትዮጵያዊ አንድነት ላይ ያለ አመለካከትን በተመለከተ የጋራ አቋም እንዲያዝ፤ በህዝቦች ሰላም ዙሪያ ቅድሚያ ተሰጥቶ እንዲሰራ እና የሴራ ፖለቲካ ህዝብን እየጎዳ በመሆኑ ከዚህ ችግር መላቀቅና የፖለቲካ አካሄድን ማስተካከል እንደሚገባ በውይይታቸው ማንሳታቸውን አቶ ንጉሱ ተናግረዋል።
በሁለቱ ክልሎች መካከል የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች በጉልበት እየተከናወኑ መሆኑን ያነሱት ፓርቲዎቹ፤ የህዝብን አንድነትና ትብብር የሚጎዱ ድርጊቶች እንዲቆሙ፤ ህግንና ስርአትን ማስከበርም የሁሉም ፓርቲዎች ጉዳይ መሆኑን በውይይቱ ስለማንሳታቸው ተነግሯል።
ወጣቱ ለአብሮነትና ለሰላም በጋራ እንዳይቆም፤ አለፍ ሲልም ህይወት እንዲጠፋና ንብረት እንዲወድም እየተደረገ ያለው ተግባር እንዲቆም ፓርቲዎቹ ማንሳታቸውን አቶ ንጉሱ ተናግረዋል።
ህግንና ስርአትን ማስከበር፤ የኅብረተሰቡ ሰላም እንዲጠበቅ ማድረግና የህብረተሰቡን ሞራል ከሚነኩ ንግግሮች መቆጠብ ፓርቲዎቹ በቀጣይ በሚያከናውኗቸው አቅጣጫዎች ውስጥ ትኩረት የሚሰጣቸው መሆኑንም አቶ ንጉሱ ጨምረው ገልፀዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 5/2012
ድልነሳ ምንውየለት
ፎቶ፡- ሐዱሽ አብረሃ