አዲስ አበባ፡- ከለውጡ በኋላ በፍትህ ሥርዓትና ዳኝነት ላይ በሚሰራው ሥራ ምንም አይነት የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት አለመኖሩን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ አስታወቁ።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት፤ ዳኞች ከስጋት ውጪ ሆነው ጫና እንደማይኖርባቸው ተማምነው እና ችግር አይፈጠርብንም ብለው በመስራት ላይ ናቸው። በዚህም “ምንም ዓይነት የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት እንደሌለ አፌን ሞልቼ መናገር እችላለሁ” ብለዋል።
“ከዳኞች ጋር ስገናኝ ‘አሁን ነፃ ሆነን ህጉን ተከትለን እየሰራን ነው’ ይሉኛል።” ያሉት ወይዘሮ መዓዛ፤ ይህ ትልቅ ውጤት ነው። ጋዜጠኞችም ሆኑ ሌሎች ኢትዮጵያውያን የጎደለውን ብቻ ሳይሆን እየተገኘ ያለውን እንደዚህ አይነት ትልልቅ ድል መጠቀም እንደሚገባቸው ተናግረዋል። “መዘንጋት የሌለበት ግን ነፃነት ውጫዊ እና ውስጣዊ ነው። ከዚህ አንጻር አንዳንድ ጊዜ አብሮ የቆየን ነገር ከውስጥ ለማውጣት የመቸገር ሁኔታ ይስተዋላል” ብለዋል።
እንደፕሬዚዳንቷ ገለፃ፤ “ነፃነቱን ወደሌላ ፅንፍ የሚወስዱና ከመንገድ የሚወጡ ያጋጥማሉ። ስለዚህ ይህንን ወደተሟላና በህግ ብቻ የመመራት ደረጃ ለማድረስ፤ እንዲሁም ጥራትን ለማረጋገጥ ከዳኞች ሹመት ጀምሮ እየተሰራ ነው። የተሻሉ ሰዎችን የመሾሙ ሁኔታ ሲያድግ በራሱ የሚተማመን ስለሚበዛ የተሻለ ውጤት ይመዘገባል።” ብለዋል።
አያይዘውም፤ “በአንድ በኩል ህግ ይከበር ይባላል በሌላ በኩል ደግሞ ያለአግባብ ሰዎች መያዛቸው ይገለፃል። ፍርድ ቤቶች የሚታገሉት በዚህ መካከል ነው። የፍትህ ሥርዓቱ በተለይ የዳኝነቱ ዘርፍ ሆነ ተብሎም ሆነ በሌላ ምክንያት ተረስቶ የቆየ ነው። መሰረተ ልማት አልተሟላለትም። እነዚህ ሁሉ ጫናዎች እያሉ ደግሞ አዲስ ችግር መጥቷል።
በመገናኛ ብዙሃን እንደሚገለፀው እስከ አራት ሺህ ሰዎች ተይዘዋል። በነበረው መዝገብ ላይ ይህ ሲደረብ ዳኞች ላይ የሚፈጥረው ጫና ከባድ ነው። ያም ቢሆን ይህንን ፈተና ማለፍ አይከብደም። ነገር ግን ህብረተሰቡም ዳኞችን ለማገዝ ፈቃደኛ መሆን አለበት” በማለት ጥሪ አስተላለፈዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 5/2012
ምህረት ሞገስ
ፎቶ፡- ፀሐይ ንጉሤ