አዲስ አበባ፡- ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ሥርዓት በተግባር አልነበረም ሲሉ የኦዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ታዬ ደንደአ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከምትታተመው ዘመን መጽሄት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ገለጹ።
አቶ ታዬ “ባለፉት 27 ዓመታት በአማራና ኦሮሚያ ክልልም ሆነ በአጋር ድርጅቶች ዘንድ የድርጅት ሊቀመንበር ማን ይሁን የሚለውን የሚወስነው ማን እንደነበር ይታወቃል። ይሁንና ‹በፊት ፌዴራሊዝም ነበር አሁን ሊፈርስ ነው፤ የብሔረሰቦች መብት ይከበር ነበር አሁን ወደ ኋላ ሊመለስ ነው› የሚል ቅስቀሳና ድራማ እየተሠራ ነውም” ብለዋል።
“በተጨባጭ ፌዴራሊዝም አልነበረም ሕገ መንግሥቱም በተግባር ሲከበር አልታየም። የብሄር ብሔረሰቦች መብትም ምናባዊ እንጂ ተጨባጭ አልነበረም። በሕገ መንግሥቱ እጅግ ወሳኝ ሰብአዊ መብቶች ተቀምጠውበታል ነገር ግን ሰዎች ሲኮላሹና ያለጥፋታቸው በሐሳብ ምክንያት ብቻ ይታሰሩ ነበር። እኔ ለዚያ ምስክር ነኝ” ሲሉም አክለዋል።
አፈና ላይ ነበረን። አሁን የለውጡ መንግሥት የታፈነውን ሲከፍተው ፈነዳ፤ ፈንድቶ ግን አላመለጠም። መንግሥት እያስታመመና እያስታገሰ እዚህ ድረስ መጥቷል። ይሄንን ግልጽ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉም ተናግረዋል። የአቶ ታዬ ደንደአን ሙሉ ቃለ ምልልስ በዘመን መጽሄት የጥቅምት 2012 ዓ/ም ዕትም ላይ ያገኙታል።
አዲስ ዘመን ህዳር 5/2012
በጋዜጣው ሪፖርተር