አዲስ አበባ፡-የኢህአዴግ ውህደት ድርጅቱ ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረውና የመላ ኢትዮጵያውያን ፓርቲ እንዲሆን የሚያደርግ መሆኑን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ገለፀ፡፡
የፓርቲው ማዕከላዊ ፅህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብርሃም አለኸኝ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደተናገሩት፤ የድርጅቱ ወደውህደት መምጣት የኢህአዴግ ማህበራዊ መሰረት እንዲሰፋና ያለምንም ልዩነት ግለሰብ አባላት እንዲኖሩት ያስችላል፡፡
ድርጅቱ እስከአሁን የአራት ብሔራዊ ድርጅቶች የበላይነት ብቻ የሚንፀባረቅበት ነው፡፡ አጋር የሚባሉ አምስት ብሔራዊ ድርጅቶች እንደአገር ድርሻ ቢኖራቸውም በኢህአዴግ ውስጥ የሚሳተፉበት ሁኔታ የለም፡፡ አልፎ አልፎ በማዕከል ደረጃ ሲፈቀድላቸው ከመግባት ውጪ መረጃና አቅጣጫ ከኢህአዴግ መቀበል ላይ ብቻ ተወስነው ምንም ዓይነት ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዳያደርጉ ተገድበዋል። ይህንን የማግለል ችግርም የድርጅቱ ውህደት ይፈታዋል ብለዋል።
እንደ አቶ አብርሃም ገለፃ፤ አጋር ድርጅቶቹ በማዕከላዊ ደረጃ የነበራቸው ተሳትፎ የተገደበ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሆነው ከአራቱ ብሔራዊ ድርጅት የተወከለ ሰው ብቻ ነበር። ከሶማሌ፣ ከአፋር፣ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ከጋምቤላና ከሐረር ጠቅላይ ሚኒስትር አይወጣም። ሰው በአገሩ ላይ መሪ የመሆን መብት ሊኖረው ሲገባ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የተሟላ ተሳትፎ እንዳይኖራቸው ተገድበዋል። ይህንን ውስንነትም የኢህአዴግ ውህደት ይፈታዋል። ስለዚህ ውህደቱ ማንኛውም ኢትዮጵያ ተስፋ ኖሮት አቅሙን እያጎለበተ ህልሙን የሚያሳካበትን ነባራዊ ሁኔታ ይፈጥራል። ይህ ደግሞ ከማህበረሰባዊ ጤንነት አኳያ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል።
በተጨማሪ፤ ኢህአዴግ እስከአሁን ድረስ አራት ብሔራዊ ድርጅቶችን በአባልነት ይዞ ተቀምጧል። የግለሰብ አባል የለውም። ግለሰቦች የድርጅቶቻቸው አባል ይሆናሉ እንጂ ለኢህአዴግ በቀጥታ አባል የመሆን ዕድል የላቸውም። አሁን ግን ውህደቱ ሲረጋገጥ ከየትኛውም ብሔር የተወለደ ሰው የትኛውንም አይነት ማህበራዊ ተሳትፎ ቢኖረውም ኢህአዴግ የተቀበለውን ፕሮግራም ከተቀበለ በቀጥታ የኢህአዴግ አባል እና ቀጥተኛ ተሳታፊ እንደሚሆን ተናግረዋል።
“እስከአሁን ድረስ በብሔራዊ ድርጅት ደረጃ በተግባቦት ላይ የተመሰረተ አመራር እየተረጋገጠ ቢሆንም፤ በተሟላ መንገድ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ተረጋግጧል ማለት አይቻልም።” በማለት የሚናገሩት አቶ አብርሃም፤ ዴሞክራሲያዊ የእርስ በርስ ግንኙነትን ፈጥሮ በብዙሃን ድምፅ ተፈፃሚነት የሚያገኝበት የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዳልነበር አስታውሰዋል።
አንዳንድ አቅጣጫዎች በኢህአዴግ ደረጃ ሲሰጡ ለኢህአዴግ ማዕከላዊነት የሚገዙ ድርጅቶች አቅጣጫውን የሚያከብሩበት ሁኔታ ሲኖር፤ ለኢህአዴግ ማዕከላዊነት የማይገዙና ኢህአዴግ በሚሰጠው አቅጣጫ አልተስማማንም ወይም ጥቅማችን አልተከበረም የሚሉ አካላት ሲኖሩ ደግሞ ከአቅጣጫው በተቃራኒ የሚሄዱበት ሁኔታ እንደነበር አስታውሰው፤ ይህ ከባለቤትነት ስሜት ጋር የሚያያዝ መሆኑን ተናግረዋል።
“ኢህአዴግን ባለቤት ስናደርገው በኃላፊነት ደረጃ ወስደን በባለቤትነት እንፈፅመዋለን። ኢህአዴግን ባለቤት ሳናደርገው ስንቀር ደግሞ እንደፍላጎታችን አቅጣጫዎችን የማንቀበልበት ሁኔታ እንፈጥራለን።” ካሉ በኋላ፤ “ኢህአዴግ አንድ ከሆነ ግን ምክንያት ይጠፋል። ኢህአዴግ የጋራ ፓርቲ በመሆኑ በግለሰብም ሆነ በቡድን ደረጃ የራስ ፓርቲ በመሆኑ ምንም ዓይነት ልዩነት ሳይኖር አቅጣጫዎች ይፈፀማሉ” ብለዋል።
እንደአቶ አብርሃም ገለፃ፤ እስከ አሁን ድረስ መሪ ሆነው የአማራን ህዝብ የሚያስተዳድሩት አማራዎች ብቻ ናቸው። ይህ በኦሮሚያም ነበር። ይህ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብትን ጠብቆ ከእርሱ ጋር ምንም አይነት ግጭት ሳይኖር፤ ነገር ግን በመሪነት ደረጃ ቋንቋውን ባህሉን ካወቁትና አስተሳሰቡን ከተረዱት ወደሌሎች አካባቢዎች መሪዎች እንዲንቀሳቀሱ በር ይከፍታል። በኢህአዴግ ውስጥ ያሉ አመራሮች የኢትዮጵያ ህዝብና የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ አመራሮች ናቸው። ስለዚህ የአካባቢውን ቋንቋና ባህል እስከተቀበሉ ድረስ በአመራርነት ቦታና አካባቢ የማይወስንበትን ነባራዊ ሁኔታ ይፈጠራል ብለዋል።
ውህደቱ ከህገመንግስቱ ውጪ ከነበረው የኢህአዴግ መዋቅራዊ አሰራር ላይ አንዳንዶች የነበራቸውን የመብት ልዩነት በማስተካከል የኢሕአዴግን ህገመንግስታዊ ተቃርኖ በመፍታት ወደትክክለኛ ህገመንግስታዊና የፌዴራሊዝም ሥርዓት ለማምጣት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ተብሎ ይታሰባል ብለዋል። “ይሄ ውህደት ከአህዳዊነትና ከጠቅላይነት ጋር የሚያያይዘው አንዳችም ምክንያት የለውም” የሚሉት አቶ አብርሃም፤ ይህንን የሚሉ አካላት “በኔ ሳንባ ተንፍሱ” የሚል ፖለቲካዊ ዕብሪት ያለባቸው ብቻ ናቸው ብለዋል።
ከአሁን በፊት “አንድ ፓርቲ እንመስርት፤ ሁሉንም ብሔራዊ ድርጅቶች እናሳትፍ፤ ኢህአዴግን ህዝባዊ እናድርግ የሚል ተደጋጋሚ ጥያቄ በማዕከላዊ ኮሚቴም ሆነ በጠቅላላ ጉባኤ ደረጃ ሲጠየቅ ነበር። አቅጣጫም ተቀምጦበታል፤ የፖለቲካ አመራሮችም በመርህ ደረጃ ተቀብለውት አልፈዋል፤ ያልተቀበለ አመራር አልነበረም።” የሚሉት ኃላፊው፤ ሲንከባለል የነበረ ጥያቄ በጥናት ይመለሳል፤ ጊዜ ያስፈልጋል ከማለት ውጪ ምንም አይነት ተቃውሞ ያልነበረበትን ውህደት ዛሬ “ጠቅላይ ነው” የሚሉት ለውጡ ገፍቶናል የሚሉ አካላት የለውጡ አመራሮች የሚወስኑትን ላለመቀበል እንጂ ሃሳባቸው ውሃ የሚያነሳ አለመሆኑን አብራርተዋል።
“ጠቅላይ ማን ነው? ተጠቅላይስ ማን ነው?” የሚል ጥያቄ ያቀረቡት አቶ አብረሃም፤ ለመጠቅለልም ፍላጎት ያለው ሊጠቀልልም አቅም ያለው አካል አለመኖሩን ተናግረዋል። 110 ሚሊዮን ህዝብ ላላት ኢትዮጵያ የሚበጃት ፌዴራሊዝም ነው በሚለው ላይ ምንም ብዥታ አለመኖሩንም ተናግረዋል።
በድርጅቱ መስመር ላይም የ“አብዮታዊ ዴሞክራሲ” ጉዳይ አከራካሪ መሆኑንና ከሞላ ጎደል የለውጥ ሃይሉ ጊዜ ያለፈበት የፖለቲካ አስተሳሰብ ነው ብሎ እንደሚያምን በማመልከት፤ የትግል ጊዜንና የስልጣን ዘመንን ጨምሮ ለግማሽ ምዕተ ዓመታት የቆየው “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” ይቀጥል ቢባልም ነባራዊው የህዝቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ፤ እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ የማያስኬድ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢህአዴግ ውህድ ፓርቲ አስተሳሰብ አንዱ የፕሮግራም ለውጥ ማምጣት ነው ሲባል፤ አብዮታዊ ዴሞክራሲ በሌላ የዴሞክራሲ አተያይ ይቀየራል ማለት መሆኑንም ተናግረዋል። ይህ ማለት በውህደቱ ወቅት ፕሮግራሙ ተጀምሮ ይጠናቀቃል ማለት እንዳልሆነ ግን አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 5/2012
ምህረት ሞገስ