• ከሁለት ሚሊዮን በላይ መራጮች ተመዝግበዋል
አለታ ወንዶ፡- ለሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ድምጽ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን የሲዳማ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ እስከ ህዳር 3 ቀን 2012 ዓ.ም ከሁለት ሚሊዮን በላይ መራጮች ድምጽ ለመስጠት መመዝገባቸውን አስታውቋል፡፡ በአለታ ወንዶ ከተማ ጨፌ ቀበሌ ጽህፈት ቤት ምርጫ ጣቢያ የተመዘገበው ወጣት እንዳሻው አበበ እንደተናገረው፤ እስካሁን በአገራዊ ምርጫም ሆነ በህዝበ ውሳኔ ላይ ድምጽ ሰጥቶ አያውቅም።የምርጫ ካርድ ለመውሰድ በጉጉት ሲጠባበቅ የነበረ ቢሆንም በስራ ምክንያት ከከተማዋ ወጥቶ ካርድ ሳይወስድ ቆይቷል። አሁን ግን ከሄደበት በመመለስ ታሪካዊ ለሆነው ህዝበ ውሳኔ ካርድ ወስዷል፡፡
ድምጹን ለመስጠትም ህዳር 10/2012ን በጉጉት እየጠበቀ መሆኑን ገልፆ፤ ህዝበ ውሳኔው ያለምንም እንከን እንዲጠናቀቅ የበኩሉን ለመወጣት ዝግጁ እንደሆነ ተናግሯል። በአለታ ወንዶ ከተማ የዴላ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ገብረመድህን ወልዱ በበኩላቸው፤ ምዝገባው እንደተጀመረ ከነቤተሰባቸው የድምጽ መስጫ ካርድ መውሰዳቸውንና ህዳር 10ን በጉጉት እየተጠባበቁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
“የድምጽ አሰጣጡ ያለችግር እንዲጠናቀቅ ህዝቡ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል” ያሉት አቶ ገብረ መድህን፤ በተለይም ወጣቶች ለጠብ ከሚጋብዙ ነገሮች ራሳቸውን በማራቅ ህዝበ ውሳኔው በሰላም እንዲጠናቀቅ ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።
የህዝበ ውሳኔውን አፈጻጸም ለማስተባበር ከአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ክልል ከሰበታ ከተማ የሄዱት አቶ ጫጮ ሲኖ በአለታ ወንዶ ከተማ የሸይቻ 02 የምርጫ ጣቢያ አስተባባሪ ናቸው። በጣቢያው 850 መራጮችን ለመመዝገብ ታቅዶ እስከአሁን አስፈላጊ መስፈርቶችን ያሟሉ 872 ሰዎች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።ይህም ህዝቡ ፍላጎቱን ለመግለጽ በከፍተኛ ጉጉት ላይ እንደሆነ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
የድምጽ ሰጪዎች ምዝገባ በጥሩ ሁኔታ ሲካሄድ መቆየቱን የተናገሩት አቶ ጫጮ፤ የከተማዋ ህዝብና የጸጥታ ሀይሉ ያደረጉት ትብብር ከፍተኛ አስተዋጽዖ ነበረው ብለዋል።ህዝበ ውሳኔው እስኪጠናቀቅም ይህ በጎ ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
የአለታ ወንዶ ከተማ ከንቲባ ተወካይ አቶ ፍሬው ዓለሙ እንደተናገሩት፤ የድምጽ ሰጪዎች ምዝገባ ሂደት ያለችግር ሲከናወን ስምንተኛ ቀኑን መያዙንና በህዝበ ውሳኔው ድምጽ ለመስጠት 21 ሺህ 676 ሰዎች ይመዘገባሉ ተብሎ ታቅዶ እስከአሁን 22 ሺህ 92 ሰዎች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
በከተማዋ በ18 የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ፍሬው፤ በመጀመሪያው ቀን ከመራጮቹ ከ50 በመቶ በላይ መመዝገባቸውንና በአሁኑ ወቅት አብዛኛዎቹ መራጮች ካርድ ወስደው የድምጽ መስጫውን ቀን በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ አብራርተዋል።በተለያዩ ምክንያቶች ከከተማዋ ራቅ ብለው የሄዱ ነዋሪዎች መጥተው ካርድ እየወሰዱ መሆናቸውንም አክለዋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የህዝብ ግንኙነት አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ እንደተናገሩት፤ እስካሁን ከሁለት ሚሊዮን በላይ መራጮች ድምጽ ለመስጠት የተመዘገቡ ሲሆን፤ ቁጥሩ እስከሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሊደርስ ይችላል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።
በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች በመጀመሪያዎቹ ቀናት የመራጮቹ ቁጥር ከተጠበቀው በላይ በመሆኑና ካርድ በፍጥነት ባለመድረሱ እጥረት አጋጥሞ የነበረ ቢሆንም፤ በአካባቢው ከሚገኙ ማስተባበሪያ ጣቢያዎች በአፋጣኝ እንዲቀርብ ተደርጎ ችግሩ መቀረፉን ተናግረዋል። እንደአማካሪዋ ማብራሪያ፤ በአሁኑ ወቅት የድምጽ መስጫ ኮሮጆዎች ወደየምርጫ ጣቢያ ዎች እየተጓጓዙ መሆኑንም አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 5/2012
መላኩ አሮሴ