አዲስ አበባ፡- (ኤፍ ቢ ሲ) መንግሥት በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ በዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከል የሚያሳየው ትዕግስት ልክና ገደብ ሊኖረው እንደሚገባ የሃይማኖት መሪዎች አሳሰቡ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከሃይማኖት መሪዎች ጋር ትላንት ባካሄደው ውይይት ላይ እንደተገለፀው መንግስት የዜጎችን ሰላም የመጠበቅና ከጥቃት የመከላከል ሚናውን ሊወጣ ይገባል።በውይይቱ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂምን ጨምሮ ከተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት የተውጣጡ የሃይማኖት መሪዎች ተሳትፈዋል።
እንደፋና ብሮድካስቲንግ ዘገባ፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ያለችበት ሁኔታ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የሚኖሩትን ዜጎች በእጅጉ እያሳሰበ መሆኑ በውይይቱ ተመላክቷል።በተለያዩ አካባቢዎች በሚቀሰቀሱ ግጭቶች ምክንያት የሰዎች ህይወት እየጠፋ እና ቤተ እምነቶች እየተቃጠሉ መሆኑም ተገልጿል።
ስለሆነም በዜጎች መካከል የነበሩትን አብሮ የመኖር፣ የመተሳሰብ እና የመቻቻል እሴቶች ለማጠናከር ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ የሃይማኖት መሪዎቹ አሳስበዋል።
በዜጎችና በቤተ እምነቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት ለመቆጣጠርም መንግሥት በጥፋት ሃይሎች ላይ ርምጃ ለመውሰድ የሚያሳየው ትዕግስት ልክ እና ገደብ ሊኖረው እንደሚገባም ጠቁመዋል። በህዝቦች መካከል ልዩነት በመፍጠር በዜጎች ህይወት ላይ እየተጫወቱ የሚገኙ አካላት ላይ የማያዳግም ርምጃ መወሰድ ይገባልም ተብሏል።
በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋለውን የፀጥታ ችግር ለመፍታትና ሁኔታዎችን ወደነበሩበት ለመመለስ እና ዜጎች በነፃነት ተንቀሳቅሰው የመስራት እና የመኖር መብታቸውን ለማስከበር መንግሥት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት የህግ የበላይነትን ማስከበር እንደሚገባውም አጽንኦት ተሰጥቷል።
የፌዴሬሽን ምክርቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም በበኩላቸው፤ ምክር ቤቱ ከፊታችን ህዳር 6 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ወር የሚቀጥል ሀገር አቀፍ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማጠናከሪያ መድረክ የሚያካሂድ መሆኑን ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተፈጠሩትን ግጭቶች በመፍታት የህዝቦችን አንድነትና መተሳሰብ ለማጠናከር የሚሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የሃይማኖት መሪዎችም ለየእምነት ተከታዮቻቸው ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ስለሰላም እና ስለአንድነት፤ እንዲሁም ስለመቻቻል አስፈላጊነት ግንዛቤ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 5/2012
ተገኝ ብሩ