አዲስ አበባ፤- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገና የተቋቋመበትን አዋጅ ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ በአስር ተቃውሞና በአስር ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጸደቀ።
ምክር ቤቱ በትናንት የ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባው ያጸደቀው ማሻሻያ የተቋሙ ቦርድ የሠራተኞችን ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም፤ ተያያዠ የሰው ሀይል፤ እንዲሁም የፋይናንስና በጀት ሁኔታዎችን በተመለከተ ለመምራት፤ ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግ፤ ለመወሰን የሚያስችለው እንደሆነ የህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አበበ ጎዴቦ ተናግረዋል።
ከዚህ በፊት የድርጅቱን ሠራተኞች፤ የበላይ ኃላፊዎችን ጨምሮ ደመወዝና ጥቅማጥቅም የመወሰን ስልጣን የተሰጠው ለምክር ቤቱ እንደነበር የተናገሩት ሰብሳቢው፤ ምክር ቤቱ እንደዚህ አይነት ስራዎችን ለመስራት ልምድና አደረጃጀት የሌለው በመሆኑ ለአፈጻጸም አዳጋች ሆኖ በመቆየቱ ማሻሻያ ማድረጉ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል። የተቋሙ ሠራተኞች በከፊል በቦርድና በሲቪል ሰርቪስ ሲተዳደሩ የነበሩ በመሆኑ የተለያየ የደመወዝ መጠን ይከፈላቸው ስለነበር ለቅሬታ ምንጭ እንደነበርም አስታውሰዋል።
በመሆኑም፤ ኃላፊነቱን ለድርጅቱ ቦርድ በመስጠት የሀገርን አቅምና ጥቅም ባገናዘበ መልኩ እየሠራ መሆኑን ምክር ቤቱ እንዲቆጣጠር ማድረጉ ከጊዜና ካመቺነት አንጻር ተመራጭ ሆኖ ስለተገኘ፤ እንደገና ማቋቋሚያ አዋጁን በማሻሻል ከሠራተኞች የደመወዝና ጥቅማጥቅም አወሳሰን ጋር በተያያዘ የኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪነትና ውጤታማነት ታሳቢ ባደረገ መልኩ ቦርዱ ውሳኔ እንዲሰጥ ስልጣን መሰጠቱን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ፤ ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ በዘጠኝ ተቃውሞና በ12 ድምጸ ተአቅቦ አጽድቋል። የአገልግሎቱ ተጠሪነት ለተወካዮች ምክር ቤት እንዲሆንና የሠራተኞች ደመወዝና ጥቅማጥቅም በምክር ቤቱ እንዲወሰን ተደንግጓል። ሆኖም፤ አዋጁ ወደስራ ሲገባ በምክር ቤቱ በኩል ደመወዝና ጥቅማጥቅም ለመወሰን ተጨባጭ ችግሮች በማጋጠማቸው አዋጁን ማሻሻል ተገቢ ሆኗል።
በተጨማሪም፤ ምክር ቤቱ የፌዴራል ድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ክፍፍል ስርዓትና ተቋማዊ አደረጃጀት ለመወሰን የቀረበ ረቂቅ አዋጅ፤ እንዲሁም በኢትዮጵያና በጅቡቲ ሪፐብሊክ መንግሥታት መካከል የተፈጥሮ ጋዝ ቧንቧ መስመር ለማስተላለፍ የተደረገውን ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል።
አዲስ ዘመን ህዳር 5/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ