በአንድ ወቅት በኤርትራ ቴሌቪዥን ‹ሮማይ› በተሰኘ ፊልም ውስጥ አንዲት ሴት ገጸ ባህሪ መሬት ላይ ተዘርራ አንገቷ በፋስ ተቆርጦ የሚያሳይ ትዕይንት አለ፡፡ ሰሞኑን በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የተከሰተውን የተማሪዎች ግጭት መነሻ በማድረግ ምስሉን በማቀናበር ድርጊቱ በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ በምትማር አንዲት የኦሮሞ ተወላጅ ተማሪ ላይ እንደተፈጸመ አስመስሎ ለማሳየት ተሞክሯል፡፡
በሌላ በኩል በህንድ ሀገር የተፈጸመና በአንዲት እንስት ላይ ጥቃት ሲደርስ የሚያሳይ ምስል በመለጠፍ በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ በኦሮሞ ተማሪ ላይ የተደረገ ግድያ ሆኖ ቀርቧል፡፡ በዚህ መንገድ በማህበራዊ ሚዲያ የሚቀርቡ ሀሰተኛ መረጃዎች ህዝብን ከህዝብ ከማጫረስ ባለፈ ምን ፋይዳ አላቸው? ድርጊቱን የሚፈጽሙትስ እነማን ናቸው? ለምን ዓላማ? በዚህ ሳቢያ የሚከሰትን እልቂት ለመከላከል ከህዝብና ከመንግሥት ምን ይጠበቃል?
አቶ ወራቅሳ ዲነግዴ ብዙውን ጊዜ በማህበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማጋለጥ ይታወቃሉ፡፡ እኚህ ሰው እንደሚሉት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ዋልታ ረገጥ አመለካከቶች አንዱ መገለጫ ሀሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግሮችን በመለጠፍ የአሸናፊነት አመለካከትን ማንጸባረቅ ነው፡፡
ሀሰተኛ መረጃ በማህበራዊ ሚዲያ ውስጥ አራት ማስተላለፊያ መንገዶች እንዳሉትም ይናገራሉ፡፡ በጽሁፍ፣ በፎቶ፣ በቪዲዮ እና የተለያዩ ሊንኮችን በመጠቀም የሚፈጸም ሲሆን ከእነዚህም መጀመሪያ ሳቢ የሚባሉት ምስልና ቪዲዮ ናቸው፡፡ አመቺነት ያለው ደግሞ ምስል /ፎቶ በመሆኑ ከእነዚህ ውስጥ አሰቃቂ ወንጀል የተፈጸመበትን ድርጊት ከኢንተርኔት ፈልጎ በማውጣትና በሚፈልጉት መንገድ በማዘጋጀት ከተፈጠረው ችግር ጋር በማቀራረብና በማዛመድ ጉዳዩን ያጦዙታል ይላሉ፡፡
ድርጊቱ የሚፈጸመው መንግሥት የጀመረውን የለውጥ ሂደት እንዳያስቀጥል ከማድረግ ነው፡፡ በሚነዙት ሀሰተኛ መረጃም ሰዎች በቶሎ እንዲናደዱና የጥላቻ መንፈስ እንዲፈጥሩ፣ ህዝብ እርስ በርሱ እንዲጠላላና እንዲፈራራ፣ እንዳይተማመን ፤ ሀገር አንድ ሆና እንዳትቀጥል እና እንድትፈራርስ በተያዘው እቅድ ነው ሲሉ ፤መሰረቱም ከተሸናፊነት ስሜት የሚመነጭ ነው ብለውታል፡፡
አቶ ሞቲ ኦሮ ናቸው፤ እንደ እርሳቸው አባባል ሀሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግር ከዕለት ወደ ዕለት የሀገሪቱን የሰላም ሁኔታ እያናጋ መሆኑን ገልጸዋል:: በሌላ ሀገር የተፈጸሙ ወንጀሎችን ምስልና ቪዲዮ እዚህ ሀገር የተደረገ አስመስለው በማቅረብ በህዝቦች መካከል ግጭት እንዲፈጠር የሚያደርጉ ሁኔታዎች መባባሳቸውን ይናገራሉ፡፡ በተለይ ሰሞኑን በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች መካከል የተፈጠረውን ግጭት ለማባባስና ወደሌሎች አካባቢዎች ለማሰራጨት ብዙ ሀሰተኛ ፎቶዎች እየተቀናበሩ መቅረባቸውን ይገልፃሉ:: ዓላማውም ለውጡን ለመቀልበስ እና በአቋራጭ ወደ ስልጣን ለመምጣት ከማለም ነው ይላሉ፡፡
ሀሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግርን ማሰራጨት በሀገር ላይ ብዙ ጉዳቶችን ሊያስከትል እንደሚችልም ጠቅሰዋል፡፡ በህዝቦች መካከል ቅራኔ እና ጥርጣሬ በመፍጠር መልካም ግንኙነትን ያሻክራል፤ በዚህ ሳቢያ ኢኮኖሚያዊ ትስስሩ ላይ ተጽዕኖ በማሳደር በሀገር ሰላምና ዕድገት ላይ አሉታዊ ጥላ ያጠላል ፤ የህዝቦችንም በሰላም የመኖር ህልውና ይፈታተናል::
አቶ ወራቅሳ ወጣቶች የትኛውንም የሚያናድዱ ምስሎች ወይም ጽሁፎች ሲያዩ መጀመሪያ ያሉንን እሴቶች ተጠቅመው ራሳቸውን ማረጋጋት ይኖርባቸዋል ሲሉ መክረዋል፡፡ ለምሳሌ በኦሮሞ ባህል ‹‹ ዱቢን ሀቡልቱ›› ይባላል፡፡ ይህ ማለት ለጉዳዩ አፋጣኝ ምላሽ ከመስጠት በፊት ጉዳዩን አቆይቶ በአንክሮ መመልከት የሚል ነው፡፡ ስለዚህ ጉዳዩን ጊዜ ሰጥቶ የመመልከት ጥበብን መጠቀም ያስፈልጋል፡፡
ሌላው ቴክኖሎጂን መረዳት ነው፡፡ የትኛውንም የሀሰተኛ መረጃ ማመሳከር የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን መቃኘት፤ ሲሆን የራስን ግምት ማስቀመጥ ይፈልጋል ባይ ናቸው፡፡ የተባለው ሁሉ እውነት ነው ብለን ከመቀበላችን በፊት ወደ እውነት የቀረቡ ነገሮችን መገመት እንደሚገባም አስቀምጠዋል፡፡
በሌላ በኩል መንግሥት እንዲህ አይነቱን ህገ ወጥ ድርጊት ለመቆጣጠር የሚያስችለውን አሰራር መዘርጋት ይጠበቅበታል ያሉት አቶ ወራቅሳ ጧትና ማታ ሀሰተኛ መረጃ የሚያሠራጩ ሀገር ውስጥም ሆነ ውጭ የሚገኙ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰድም ማስወሰድም ይኖርበታል፡፡ የመንግሥት ሚዲያዎችን በመጠቀም የሀሰተኛ መረጃዎችና የጥላቻ ንግግሮችን በማጋለጥ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ይገባል ብለዋል፡፡
አቶ ሞቲ በበኩላቸው ወጣቱ ከምንም በላይ ማየት የሚገባው የሀገሩን ህልውና መጠበቅ ነው:: ሰላም ቢናጋ ህዝብ ችግር ውስጥ ይወድቃል፤ እጣ ፈንታችን ምን ሊሆን እንደሚችል ቆም ብሎ ማሰብ ይገባል ሲሉ መክረዋል፡፡
አንድን የፈጠራ ወሬ እውነት አድርጎ ከመቀበል በፊት የመረጃውን እውነተኝነት በሰከነ መንፈስ ለማረጋገጥ መሞከር ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ የሀሰተኛ ወሬዎች እውነት ቢሆኑ እንኳን ችግሩን ማርገብ እንጂ ያንን ለመበቀል መነሳሳት ተገቢ አይደለም፡፡ ወጣቱ የሀሰተኛ ወሬዎችና ምስሎች ሲለቀቁ ከዚያ ድርጊት ጀርባ ያለው ማን ነው? ለምን ዓላማ ተለቀቀ? ብሎ ሁኔታውን መረዳት ይጠበቅበታል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅም4/2012
ኢያሱ መሰለ