አዲስ አበባ፡- በአገሪቱ ከ 1900 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን የቴክኖ ሞባይል አምራች ድርጅት ገለፀ፡፡
በኢትዮጵያ የቴክኖ ሞባይል ድርጅት የገበያ ልማት ሥራ አስኪያጅ ሐሳኒ ሞሀመድ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ድርጅቱ በትኩረት ከሚሠራባቸው የቴክኖሎጂ ሽግግር ተግባራት ባሻገር በአገሪቱ ለበርካቶች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ በአሁኑ ወቅት በጎሮ አይሲቲ ፓርክ ግዙፍ ፋብሪካ ሥራ የጀመረ ሲሆን፤ ይህም ከዚህ ቀደም ሲያከናውናቸው የነበሩ ተግባራትን አጠናክሮ ለማስቀጠል ያስችለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የቴክኖ ሞባይል ምርት ክፍል ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ደብል ቼን ድርጅቱ በቅርቡ ወደ ለገበያ እንደሚያቀርባቸው የተነገረላቸው የፋንተም ዘጠኝ እንዲሁም ካሞን 12 ምርቶቹን አስመልክቶ ይፋዊ ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ለመገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት፤ ድርጅቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሕብረተሰቡን ኑሮ ቀላል ለማድረግና በእንቅስቃሴውም የሕዝቦችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ አዳዲስ የስልክ ቴክኖሎጂዎችን እንደያዙ በተነገረላቸው ምርቶቹ የተሻሉ አገልግሎቶችን ይዞ ቀርቧል፡፡
ደብል ቼን፤ ድርጅቱ በእያንዳንዱ ተግባራቱ የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሥራዎችን ሲሰራ እንደቆየ አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅትም ምርቶቹ በዓለም ላይ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ግኝቶችን ይዘው ብቅ እንዳሉና ይህም አገሪቱ በተንቀሳቃሽ ስልክ አገልግሎት በዓለም ያላትን ተደራሽነትና ፉክክር እንድታሳድግ ይረዳታል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በተንቀሳቃሽ ስልክ ተደራሽነት በዓለም ሠንጠረዥ ውስጥ 45ኛ ደረጃን ይዛ እንደምትገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ዓለም የደረሰባቸውን ቴክኖሎጂዎችና የበየነ መረብ ተጠቃሚነቷ ደግሞ 79ኛ ደረጃ ላይ እንደሚያስቀምጣት፤ በዘርፉ በየዓመቱ የምታሳየው ዕድገት ግን ዝቅተኛ እንደሆነ ግሎባል ኮኔክቲቪቲ ኢንዴክስ ያወጣው መረጃ ያሳያል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 3/2012
ፍዮሪ ተወልደ