አዲስ አበባ፡- የአገር ውስጥ የባህል አልባሳት አምራቾች ከውጭ በሚመጡ ምርቶች ምክንያት ገበያቸው እየተዳከመ እንደሚገኝ ተገለፀ፡፡ የባህል አልባሳት ዲዛይን ባለቤትነት ጥበቃ አለመኖሩ ችግሩን እያባባሰ እንደሚገኝም ተጠቁሟል፡፡
በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የእደ ጥበባት ማበልፀጊያ የገበያ ልማት ዳይሬክተር አቶ ነጋሽ አስናቀ ትናንት በኢትዮጵያ የባህል ጥበብ አልባሳት ተወዳዳሪነት ላይ ያተኮረ ውይይት ሲካሄድ እንዳሉት፤ የአገር ውስጥ የባህል አልባሳት አምራቾች የሚያመርቱት ምርት ከውጭ ተሰርቶ ከሚመጣው የባህል ልብስ ጋር ተወዳዳሪ መሆን አልቻለም፡፡ ለዚህ ደግሞ የአገር ውስጥ አምራቾች የሚሸጡበት ዋጋ መጨመርና የጥሬ እቃ እጥረት ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው፡፡
እንደ አቶ ነጋሽ ገለፃ፤ የአገር ውስጥ የባህል አልባሳት አምራቾች ምርቶቻቸውን በብዛት አለማምረታቸውና በውድ ዋጋ መሸጣቸው ተጠቃሚው የቻይና ምርት የሆነውን ሽፎን እንዲገዙ አድርጓቸዋል፡፡ የባህል አልባሳት ላይ የሚሰሩት ዲዛይኖች ተመሳሳይ መሆንና በቴክኖሎጂ የተደገፉ አለመሆናቸውም በገበያው ላይ ተፈላጊነታቸውን ቀንሶታል፡፡
‹‹የባህል አልባሳትን ለማምረት ከጥጥ በስተቀር ሁሉም ጥሬ እቃ የሚገባው ከውጭ አገር ነው›› የሚሉት አቶ ነጋሽ፤ ሸማኔው ድርና ማግ ለማግኘት መቸገሩ፣ የምርት ጥራት የሚያረጋግጥ ባለሙያ አለመኖር እንዲሁም አልባሳቱን ከበዓላት ውጭ እንዲለበሱ አድርጎ አለመስራት የባህል አልባሳት አምራቾች ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ማድረጉን አመልክተዋል፡፡
በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት የእሴት ዳይሬክተር አቶ ታደሰ ወርቁ በበኩላቸው፤ በአገር ውስጥ የሚመረቱ የባህል አልባሳት ዲዛይን ጥበቃ እየተደረገለት አለመሆኑን ፤ የአልባሳቱ ዲዛይን ተመሳሳይነትና ባለቤት አልባ በመሆኑ ጥበቃ ለማድረግ አስቸጋሪ ማድረጉን እንዲሁም የባህል አልባሳትን በአዕምሯዊ ንብረትነት ጥበቃ ለማስመዝገብ ህጋዊ ማዕቀፍ አለመኖሩን አስረድተዋል፡፡
የባህል አልባሳት ዲዛይኖችን ለመጠበቅና እውቅና ለመስጠት አስቸጋሪ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለባህል ልብሶች ዲዛይን የወል የንግድ ስሞችን ለመስጠትና ከውጭ የሚገቡትን ምርቶች ለመቆጣጠር የሚያስችል ጥናት እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 3/2012
መርድ ክፍሉ