አዲስ አበባ፡- በምስረታ ላይ ያሉት የዘምዘም፣ የሂጅራ፣ የዛድና የነጃሺ እስላማዊ ባንኮች የአክሲዮን ሽያጭም ሆነ የሚሰጡት አገልግሎት ለሁሉም ዜጋ ክፍት መሆኑ ተገለጸ። የባንኮቹ የሥራ ኃላፊዎች ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ ባንኮቹ የሚሰጧቸው አገልግሎቶች የሸሪያን ህግ መሰረት ያደረጉ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በባንኮች በመስኮት ደረጃ የሚሰጡትን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶችንና ከወለድ ነፃ አገልግሎቶችን ያካተቱ ናቸው።
ባንኮቹ ወለድን ከመቀበልና ማህበራዊ ጉዳዮችን የሚጎዱ አልኮል ለማምረት፣ ለቁማርና ለጦር መሳሪያዎች ከሚውል ብድርና አገልግሎት ውጭ ሌሎች አገልግሎቶችን በሙሉ ይሰጣሉ ያሉት ኃላፊዎቹ፣ በባንኮቹ የእስልምና ተከታዮች ብቻ ሳይሆን የተለያየ እምነት ተከታይ ማህበረሰቦችም የሚገለገሉበት ነው ብለዋል።
ከወለድ ነፃ አገልግሎት በሁሉም እምነት የሚደገፍ ነው ያሉት ኃላፊዎቹ፣ የየትኛውም እምነት ተከታይ በአክሲዮን ሽያጩም ሆነ በአገልግሎቱ ተሳታፊ እንደሚሆንም አመላክተዋል።ይህም ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ከማድረጉም በላይ የባንኩን አገልግሎት ሰፊ እንደሚያደርገው አመልክተዋል።
በምስረታ ላይ ያሉት ባንኮች አደራጆች እንደገለጹት ፣ እስላማዊ ባንኮቹ በዘንድሮው በጀት ዓመት ወደ ሥራ ይገባሉ። የዘምዘም ባንክ አደራጅ አቶ ጀማል ሙዘይን በአንድ ዓመት ውስጥም 60 ቅርንጫፎችን ለመክፈት እና 800 ሰራተኞች ለመቅጠር ማቀዳቸውን ጠቁመዋል።
የነጃሽ ባንክ አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ጀማል መሀመድ እንደተናገሩት ፣ ባንኩ በሸሪያ ህግ መሰረት 43 አይነት አገልግሎቶችን የሚሰጥ ሲሆን በርካታ ቅርንጫፎችን እንደሚከፍትና በሶስት ዓመታት ውስጥ ከ3ሺ እስከ 5ሺ ሰራተኞችን ይቀጥራል ብለዋል።
የሂጅራ ባንክ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጅብሪል ዑስማን በበኩላቸው፤ በስድስት ወራት ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ቅርንጫፎች ተከፍተው ወደ ሥራ ይገባሉ። በቅርብ ጊዜም 40 ቅርንጫፎች ይከፈታሉ ሲሉ ተናግረዋል።
የዛድ ባንክ አደራጅና የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙኒር ሁሴንም በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ 70 ቅርንጫፎችን እንደሚከፍቱና በአንድ ዓመት ውስጥም 400 ሠራተኞችን እንደሚኖራቸው አመልክተዋል።
የባንክ አደራጆቹ እንደገለጹት፣ በእስካሁን የሥራ ሂደት ከህግና ከፖሊሲ ጋር የተያያዙ ክፍተቶች ፣ የግንዛቤ፣ የሰው ኃይል፣ የቴክኖሎጂና የአሰራር ስርዓት ችግሮች አጋጥመዋቸዋል።
በዓለም ላይ የእስላማዊ ባንክ ተግባራዊ መሆን የጀመረው በ1960ዎቹ ሲሆን በ50 ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ እመርታ አሳይቷል። ባለፈው ዓመት በእስላማዊ ባንኮች 2 ነጥብ 8 ትሪሊዮን ዶላር በዓለም ደረጃ ተንቀሳቅሷል። ይህም በየዓመቱ 18 በመቶም የሚያድግ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ 1ሺ300 እስላማዊ ባንኮች ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን ህዳር 3/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ