አዲስ አበባ፡- የቴሌኮም አገልግሎት የሚሰጡ ኦፕሬተሮችን ለመቆጣጠር የሚዘጋጀው ሕጋዊ ማዕቀፍ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሆኖ እንዲዘጋጅ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ባልቻ ሬባ ትናንት በሰጡት መግለጫ፣ ኦፕሬተሮችን ለመቆጣጠር የሚያስችለው ሕጋዊ ሰነድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለውና ተወዳዳሪ ማድረግ የሚያስችል ሆኖ በባለስልጣኑ እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ሕጋዊ ማዕቀፉ ሲዘጋጅ ከኮሙኒኬሽን አገልግሎት አዋጅ (አዋጅ ቁጥር 1148/2011) ጋር የተጣጣመና ለአገርና ለሕዝብ ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጥ ሆኖ እየተዘጋጀ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡
እንደእርሳቸው ገለፃ፣ የቁጥጥር ሕጉ ዝግጅቱ ከመጠናቀቁና የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃዶች ከመስጠታቸው በፊት የባለድርሻ አካላት ምክረ ሃሳቦች እንዲካተቱበት እየተደረገ ይገኛል፡፡ ባለስልጣኑ ለኦፕሬተሮች ፈቃድ ለመስጠት ጨረታ በሚያወጣበት ወቅት ከአገልግሎት አቅራቢዎቹ የሚጠበቁት ሕጋዊ ግዴታዎችና መስፈርቶች የጨረታ ሰነዶቹ ውስጥ እንዲካተቱ ይደረጋል፡፡
የቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፉን በውድድር ላይ የተመሰረተ በማድረግ ጥራት ያለው አገልግሎት ለማቅረብ ባለስልጣኑ ግልጽ ጨረታ በማውጣት የቴሌኮም አገልግሎት ለሚያቀርቡ ሁለት ኦፕሬተሮች ፈቃድ ለመስጠት እየሰራ እንደሆነ ኢንጂነር ባልቻ አስታውሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን በኮሚኒኬሽን አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 1148/2011፣ ነሐሴ 6 ቀን 2011 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን፤ ዋነኛ ተግባሩም ተወዳዳሪ የገበያ ሥርዓትን በማበረታታት የተጠቃሚዎችን ፍላጎትና ተደራሽነት ያሟላ፣ ጥራቱ የተጠበቀ ቀልጣፋ አስተማማኝ እና ኢኮኖሚያዊ አቅምን ያገናዘበ አገልግሎት በመላ ሀገሪቱ እንዲስፋፋ ማድረግ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 3/2012
አንተነህ ቸሬ