አዲስ አበባ፡- ንቁና አምራች የፋብሪካ ሠራተኞችን ለማፍራት አዳዲሶችን ከኢንዱስትሪው ጋር ለማስተዋወቅ የሚያግዝ አገራዊ የስልጠና ሰነድ ተዘጋጀ፡፡
ሰነዱን አስመልክቶ በትናንትናው ዕለት በተካሄደ የማሳያ መድረክ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅና ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሽ ለማ እንደተናገሩት፣ አገራዊ የክህሎትና የሥነ ልቦና የስልጠና ሰነድ በቪዲዮ ታግዞ የሚሰጥ ሲሆን በዘርፉ የሚሰማራው የሰው ኃይል መሰረታዊ ፍላጎቶችን ከኢንዱስትሪው ጋር ለማጣጣም ያለመ ነው፡፡
ይህም በጨርቃ ጨርቅና ልብስ ስፌት ዘርፍ የሚሰማሩ አዳዲስ ሠራተኞች ከኢንዱስትሪው ጋር በቶሎ እንዲላመዱ ሁኔታዎችን የሚያቀል ከመሆኑም ባሻገር ሠራተኛው የኢንዱስትሪ ባህል እንዲያዳብርና ንቁና አምራች እንዲሆን ያግዛል ተብሎ የታመነበት መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
ለስልጠና ሰነዱ የገንዘብ ድጋፍ ያደረገው የ“ኢንተርፕራይዝ ፓርትነርስ” ተወካይ አቶ ነቢል ቀሎ በበኩላቸው በጨርቃ ጨርቅና ልብስ ስፌት ላይ የሚሰማሩ አዳዲስና ነባር የፋብሪካ ሠራተኞችን በሥራቸው ውስጥ የሚያጋጥሟቸው የተለያዩ ተግዳሮቶችን ተቋቁመው ለራሳቸውና ለዘርፉ ዕድገት የሚጠበቅባቸውን እንዲያበረክቱ እገዛ እንደሚያደርግላቸው ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ ነቢል ገለጻ የስልጠና ሰነዱ በዋነኝነት በፋብሪካ ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ሠራተኞች ወደ ኢንዱስትሪው የሚያደርጉትን ሽግግር፣ የልብስ ስፌት ሥራ መሰረታዊ ሂደቶችን፣ በሥራቸው ውጤታማ የሚሆኑባቸው የስኬት ምስጢሮች ያካተተ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የፋብሪካ ሠራተኞች በግል ህይወታቸውም ስኬታማ እንዲሆኑ የሚያግዙ በአኗኗር ዘይቤ ላይ የሚያተኩሩ የአመጋገብ፣ የግል ንጽህና አጠባበቅ፣ የሥራ ቦታ ጤንነትና ደህንነት አጠባበቅ፣ የጊዜና ሃብት አጠቃቀም፣ የቡድን ሥራ ውጤታማነት፣ ተግባቦትና መልካም ግንኙነት የሚፈጠርባቸውንና የችግር አፈታት ዘዴዎችን በሚያሳይ መንገድ በአሥር ምዕራፎች ተከፋፍሎ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አገራዊ የስልጠና ሰነዱ ከፋብሪካዎች የሥራ ባህሪና ከሰራተኛው የሥራ ሁኔታ አኳያ ከሦስት እስከ አምስት ደቂቃ በሚሆን የጊዜ ርዝመት ሰልጣኞችን መሰረት አድርጋ በተቀረጸች “አስቴር” በተሰኘች ዋና ገጸ ባህሪ አማካኝነት በቪዲዮ እየተተረከ በቀላሉ የሚቀርብ ነው፡፡
የስልጠና ሰነዱ የተዘጋጀው በኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅና ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩትና “ኢንተርፕራይዝ ፓርትነርስ” በተባለ የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት(ዩ.ኬ.አይድ) ትብብር ሲሆን ትኩረቱን ያደረገው በጨርቃ ጨርቅና ልብስ ስፌት ኢንዱስትሪ ሠራተኞች ላይ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 3/2012
ይበል ካሳ