ምሥጢረ ብዙው ተክል
በኔ ሀገር የቀርቀሃ ዛፍ/ተክል ለቤት ጣራ፣ ለመዝጊያ፣ ለሙኸዶ፣ ለሌማት፣ለኮለላ፣ ለቅርጫት፣ ለሕፃናት መኝታ፣ ለአምፑል ማንጠልጠያነት፣ ለዕንቁላል መያዣ፣ ለፍራፍሬ ማቅረቢያነት፣ ለቆሻሻ (ልብስ)ማጠራቀሚያነት…በአጠቃላይ ለመገልገያነት በዓይነት እየተሠራ፣ በቤት ቁሳቁስነት ያገለግላል፡፡ ነገር ግን ቻይና ሀገር የሚበቅለው ቀርቀሃ፣ ከእኔው ሀገር ቀርቀሃ ጋር ተመሳሳይ ሆኖ ሳለ፣ ነገር፣ ተጨማሪና የሚገርም አገልግሎት እንደሚሰጥ በዓይኔ በብረቱ ተመለከትሁ፡፡ እንዳየሁት ከሆነ ከቻይናው ቀርቀሃ የሚሠሩት ምርቶች፣ በአንጻራዊነት ዋጋቸው ውድ ቢሆንም፣ ምቾትና ጥራት ያላቸው ስለሆኑ፣ ማንም ምርቶቹን ሳይገዛ ለማለፍ አይቻለውም፡፡
በቻይና ሀገር ቀርቀሃ ምግብ ነው፡፡ እንደምን ከተባለ ሥሩ በተለያየ መልክ እንደጎመን ተሠርቶ ወይም በሾርባ መልክ ተሰናድቶ፣በታላላቅ የገበታ ሥነ ስርዓት ላይ ይቀርባል፡፡
ቀርቀሃ ልብስ ነው፡፡ እንደምን የሚል ካለም በጣም ታላላቅ የተባሉ ዕውቅ ሴቶች በአንገታቸው ጣል የሚያደርጉት እጅግ በጣም ለስላሳ (እንደ ባለጸጉር መሳይ) ስካርፕ ሆኖ ይለበሳል፣ እሱ ራሱ እንደቀሚስም ይሆናል (እኔና ጓደኞቼ ለጉብኝት በሄድንበት ጊዜ ከተደረገልን ገለጻ፣ ዕድሉን ተጠቅመን በመግዛት፣ ይዘን ለመምጣት ችለናል)
ከቀርቀሃ የሚያማምሩ የወንድ ሸሚዞች፣ የሴቶች ቲ ሸርቶች፣ ሹራቦች፣ በሙቀት የአየር ሁኔታ እንኳን ሳይቀር፣ ሁለት ሦስት ቀን ቢለበሱ ጠረን/ ሽታ የማያመጡ የውስጥ ሱሪዎች፣ የጡት ማስያዣዎች፣… ተመርተው ተመልክተናል፡፡ እዚህ ነጥብ ላይ እኛን ጎብኝዎችንም ሆነ አስረጂዎቹን በጋራ ፈገግ ካስደረጉን ምርቶች መካከል በተለይ፣ ከቀርቀሃ ስንፈተ ወሲብ ላለባቸው ወንዶችም ሆኑ ሴቶች እንዲያገለግሉ ስለተዘጋጁት የውስጥ ሱሪዎች ማብራሪ በተሰጠበት ጊዜ ነበር፡፡
ቻይና ውስጥ ቀርቀሃ ጫማ ነው፡፡ በልዩ ሁኔታ ተዘጋጅቶ በተንጣለለው የቀርቀሃ ምርቶች መሸጫ ሱቅ ውስጥ ከሞሉት ምርቶች መካከል፣ የሴቶችና የወንዶች ጫማዎች ለዬት ያሉ መሆናቸውን ተመልክተናል፡፡ እርግጥ እነዚህም ዋጋቸው ውድ ቢሆንም፣በጣም ውብ እና ለእግር የሚመቹ ቆንጆ ጫማዎች ናቸው፡፡ ይህን ይበልጥ ያረጋገጥሁት ደግሞ የተጠየቅሁትን ዋጋ ከፍዬ የገዛሁትን ውብ ጫማ ተጫምቼ መራመድ ከጀመርሁ በኋላ ነበር፡፡
ቀርቀሃ የብዙ በሽታ መድኃኒትም ነው፡፡ ቻይናዎች ከቀርቀሃ የወገብ ሕመም ላለባቸው፣ የጉልበት ሕመም ለሚያስቸግራቸው፣ በአንገታቸው አካባቢ የሕመም ስሜት ለሚሰማቸው ሁሉ… ፈውስ የሚሰጡ የአካል ማሰሪያዎችን/ማበቻዎችን አምርተዋል፡፡
በዚህም ይህ ዓይነት ችግር ያለባቸው ሰዎች፣ እነዚህን ማሰሪያዎች/ማበቻዎች በመግዛት ድርጁ በሆነው መታጠቂያ መሀል ላይ ውሃ ያርከፈክፋሉ፤ ከዚያም ልክ አንዳንዴ ራሳችንን ህመም ሲሰማን በመቀነት ሸብ እንደምናደርገው ሁሉ በተጠቀሱት የሰውነት ክፍሎቻው አካባቢ በሚያማቸው የአካል ክፍሎች ላይ ለጥቂት ደቂቃዎች (ከ40- 50 ደቂቃ)ሸብ አድረገው ያስራሉ፤ በዚህም ፈውስ እንደሚያገኙ እዚያው ማሳያ ቤቱ(Show Room) ውስጥ እንዳለን፣ ከመካከላችን የአንገት ሕመም እንደነበረው በመግለጽ ለመሞከር ፈቃደኛ ከሆነ ጓደኛችን ለማረጋገጥ ችለን ነበር፡፡
ቻይና ውስጥ ከቀርቀሃ ተክል፣ የጸጉር ቀለም፣ የኩሽና ቤት ፈሳሽ ሳሙና፣ የመኪና ማጠቢያ ሳሙና፣ በቆሻሻ የቸከ ልብስ ማስለቀቂያ ዲተርጀንት፣ የመጠጥ ውሃን ከልዩ ልዩ «ቶክሲኮች» በፍጹም የሚያጣራ ቅመም…ሁሉ መመረቱን በአርምሞ ተመልክቻለሁ፡፡ እንግዲህ የዚህ ሁሉ ሐተታዬ ምክንያት አንድና ግልጽ ነው፡፡ ይኼውም የሚመለከታቸው አካላት በሚገባ አስበውበት፣ ኢትዮጵያውያን በቻይና ሀገር ሥልጠና እንዲያገኙ ሁኔታዎችን እንዲያመቻቹ፣ በእኛ ሀገር የሚመረተው ቀርቀሃም ይህን መሳይ ተጨማሪ አገልግሎቶች እንዲሰጥ እንዲያበቁ… ለማሳሰብ ያህል ነው፡፡
በጸሎት የተመለሰ መዓት!
በያዝነው ዓመት 2011 ዓ.ም መስከረም መግቢያ ላይ፣ ቻይና በነበርንበት ጊዜ፣ታይፉን የተባለ የውሃ ላይ አውሎ ነፋስ ድንገት በመከሰቱ፣ ፊሊፒንስን ከመታ በኋላ የምንኖርበትን ከተማ እንደሚመታ፣ ሁላችንም መስኮቶቻችንን ጥርቅም አድርገን በመዝጋት፣ ከክፍልና ከግቢ እንዳንወጣ ብሔራዊ የማስጠንቀቂያ ደወል ተደወለ/ታወጀ፡፡ አብረውን የነበሩት የሌሎች ሀገር ዜጎች፣መጣ ስለተባ ለው የሞት ድግስ ደንታ አልነበራቸውም፡፡ ከዚያው ከኤዥያ፣ ከላቲን አሜሪካና ከበሀማስ…የመጡ ስለነበሩ፣ ለክስተቱ አዲስ አልነበሩምና እንደኛ አልደነገጡም፤ ስለሁኔታው የተሸበርነው እኛ አስር ኢትዮጵያውያን እና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች የመጣን ዜጎች ብቻ ነበርን፡፡ በዚያው ሰሞን በሀገራችን በተለይ በአዲስ አበባ የተለያዩ ቦታዎች በተለይም ቡራዩ አካባቢ የወገኖቻችን ሕይወት እንደጠፋ የሰማንበት ወቅት ነበርና የበለጠ ሆድ ባሰን፡፡
ከወንድሞቻችን ጋር በመመካር፣ ባለንበትም ሆነ በሀገር ቤት ስላንዣበቡት አደጋዎች በየክፍሎቻችን ሆነን እንድንጸልይ ተነጋገርን፡፡
አርቲስት ወለላ አሰፋ፣ ገጣሚ የሽወርቅ ወልዴ እና እኔ፣ በአንዳችን ክፍል በመሆን ለተከታታይ ቀናት ጸለይን፤ ፈጣሪ ለሀገራችን ምህረት እንዲያወርድ በትኩስ ዕንባ ጭምር ጠየቅነው፡፡ ባለንበት ሀገር የተከሰተውን አደጋም እንደ ደመና ገፎ፣ እኛንም ለሀገራችን እንዲያበቃን፣ ደጋግመን ፈጣሪን በለቅሶ ጠየቅን፡፡ የ CTGN ዜና አሁንም አሁንም ውሃማው አውሎ ነፋስ ወደቻይና እየተጠጋና አንድ ትልቅ ከተማ መትቶ፣ ብዙ ሰው እንደሞተ አወራ። የኛም ጸሎት አልተቋረጠም።
ከሁለት ቀናት በኋላ፣ ታይፉን የተባለውና ውሽንፍራማው የውሃ አውሎ ነፋስ፣ እኛ የምንኖርበትን ግዛት በስተደቡብ ቻይና በመተው፣ ወደሌሎች የቻይና ግዛቶች ማለፉን ሰማን፡፡ ቀጥሎም ከምንኖርበት አስተዳደር በተሰራጨው መረጃ «ግዛታችን» ከውሃማው አውሎ ነፋስ አደጋ መትረፏን እና ሕዝቡም የተለመደ የዕለት ከዕለት ተግባሩን ያለሥጋት እንዲቀጥል ታወጀ፤ በደስታ ተቃቀፍን፤ እፎይ አልን፡፡
እንደወግና ባህላችን፣ የልብ እና የዕንባ ጸሎት፣ ለራሳችን ብቻ ሳይሆን፣ ለሌሎች ሕዝቦችም እንደሚተርፍ እምነታችንን ደግመን አጸናን፡፡ በመጨረሻም የነበርንባት የሀይናን ግዛት ከሕይወት ቀሳፊው ታይፉን ዳነች፤ እኛም ተልዕኳችንን በስኬት አጠናቀን፣ ይኼው በሕይወት ለሀገራችን አፈር በቃን፡፡
በልጅነቴ በተወለድሁበት አካባቢ ዝናም ሲዘገይ፣ ቤተ እምነቶች ሁሉ ምእመኖቻቸው እንዲጾሙ፣ እንዲጸልዩ፣ ወደ ፈጣሪያቸው እንዲያለቅሱ፣ እናቶችም ሆኑ እንስሳት ልጆቻውን ለተወሰነ ጊዜ ጡት እንዳያጠቡ፣ ባልና ሚስት፣ ፍቅረኞች ከአልጋ መውደቅ እንዲታቀቡ… ይገዘታል፡፡ ሕዝቡ የአባቶችን ምክር ተቀብሎ የታዘዘውን በጥንቃቄ ይፈጽማል፡፡ በዚህ መልክ ፈጣሪ የሁሉንም ጽኑ ኀዘን ተመልክቶ ይራራልና፣ ሳይዘገይ የተጠየቀውን፣ የተለመነውን ይቸራል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን በአንድ ልብ እና በጋራ ሆነን ከቆምን፣ የማናሸንፈው ምድራዊ ኃይል እንደሌለ፣ ያለፉት ታሪኮቻችን ምስክር ናቸው።
አዲስ ዘመን ታህሳስ21/2011
በውዳላት ገዳሙ