አዲስ አበባ፡- ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በወራሪ መጤ ዝርያዎች ቢያዝም መንግሥት ለችግሩ ትኩረት እንዳልሰጠው የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
በኢንስቲትዩቱ የአርክቦትና ጥቅም ተጋሪነት የዕጽዋት ባለሙያ አቶ ተስፋዬ በቀለ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ፤ እስካሁን ባለው መረጃ ከሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ በመጤ ዝርያው መወረሩ በሰዎች ጤና፣ በግብርና ምርት መቀነስ ፣ ስነ ምህዳርን በማዛባት ችግር እያስከተሉ ይገኛሉ ብለዋል።
እንደ አቶ ተስፋዬ ገለፃ፣ በ 2010 ዓ.ም በተሰበሰበው መረጃ መሰረት ከፍተኛ ጉዳት እያስከተሉ ካሉት መካከል ፕሮሶፒስ የተባለው መጤ ዝርያ በአፋር፣ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ድሬዳዋና ደቡብ ክልሎች ከአንድ ነጥብ 56 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬትን የወረረ ሲሆን፤ ትግራይና ሱማሌ ክልሎችን ጨምሮ ወደ ሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች እየተስፋፋ ነው።
ወራሪ መጤ ዝርያው ባለፉት 31 ዓመታት በአፋር ክልል ብቻ 18 ቢሊዮን ብር አገሪቱ እንድታጣ አድርጓል ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ ስነ ምህዳር በማዛባት፣ የእንስሳት ግጦሽና ውሃ በማጥፋት ዜጎች እንዲጋጩ መንስዔ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሌላው ወራሪ መጤ ዝርያ የእምቦጭ አርም ሲሆን፤ በጣና፣ የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች፣ በባሮ ወንዝ እና ሌሎች የውሃ አካላት ላይ ከ10ሺ146 ሄክታር መሬት በላይ ወረራ አካሂዷል ። በዚህም የውሃ መጠንን፣ የዓሳ ምርትን፣ የመስኖ እርሻን በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ አድርጓል። አረሙ በከብቶች ጤና ላይ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ በዓመት 51 ሺ 500 ቶን ዓሳ የማምረት አቅም ቢኖራትም በመጤ ዝርያው ምክንያት 31ሺ930 ቶን እንደምታጣ አቶ ተስፋዬ አብራርተዋል።
አረሙን ለማጥፋት ከፍተኛ ገንዘብ ስለሚጠይቅ አገሪቱን ለከፋ ችግር እየዳረጋት መሆኑን የተናገሩት አቶ ተስፋዬ፤ በወንጂ ሸዋ ሀይቅ ላይ ያለውን መጤ ዝርያ ለማጥፋት ለ14 ዓመታት በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ቢወጣም ማጥፋት አልተቻለም። በተመሳሳይ በጣና ሀይቅ ላይ ግማሽ ሄክታር እምቦጭ ለማጥፋት አምስት ሺ ብር ይጠይቃል።በጠቅላላው በአገሪቱ ያለውን መጤ ዝርያ በአንድ ጊዜ ለማጥፋት 125 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።
ፈርምሲሳ የተባለው ወራሪ አረም በእርሻ መሬት በውሃና በተለያዩ ቦታዎች 286 ሺ419 ሄክታር መሬትን የወረረ ሲሆን፤ አዝዕርት እንዳይበቅሉ፤ ላሞች ወተታቸው እንዲመር ፤ አበባውን ከቀሰሙ ንቦች የሚገኘው ማር ትክክለኛ ጣዕሙን እንዲቀይር ያደርጋል፡፡ በኬሚካሉ የተነካካ አዝዕርትና ስጋ የተመገበ ሰው ለኩላሊት፣ ለጉበት፣ ለአንጀትና ለአስም በሽታ እንደሚያጋልጥም አቶ ተስፋዬ ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ተስፋዬ ማብራሪያ ፤ሌላው ወራሪ ዝርያ የወፍ ቆሎ ሲሆን፤ 63 ሺ406 ሄክታር መሬት ይሸፍናል። ይህም የመሬት ስነ ምህዳርን እያዛባ ነው። በአገሪቱ 35 የሚሆኑ መጤ ዝርያዎች ያሉ ሲሆን፤ የወረሩት መሬት መጠን በትክክል አይታወቅም። እንደ ሆንቆንቆል ያሉ መርዛማ ቅጠል ያላቸውና ሌሎች አዳዲስ መጤ ዝርያዎችም እየተከሰቱ ነው። የመከላከልና አዳዲሶቹም እንዳይስፋፉ በሚፈለገው ደረጃ እየተሰራ አይደለም። በዚህም የተነሳ አገሪቱ ላይ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል ።
አገር በቀል የብዝሃ ህይወትን ከመጠቀም ይልቅ የውጭውን ዝርያ ማማተር እንወዳልን ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ በቀጣይ ወራሪ መጤ ዝርያዎች እንዳይገቡ ቁጥጥር ማድረግና መጤ ዝርያውን ለማስወገድ ተቋም አቋቁሞ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል ።
አዲስ ዘመን ህዳር 3/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ