አዲስ አበባ፡- በዛሬው ዕለት ሥራ የሚጀምረው አዲሱ ብሔራዊ የሥራ ገበያ መረጃ ስርዓት መረጃዎችን በአንድ ቋት በማስገባት በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የነበረውን የሀሰት ሪፖርት ችግር እንደሚያቃልል የኢትዮጵያ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
በኢትዮጵያ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን የተቀናጀ የመረጃ ትንተናና ሥርዓት ማበልፀጊያ ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ ሠርፀ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ መረጃዎችን አምስት የፌዴራል የመንግሥት ተቋማት ይሰበስቡ ነበር፡፡ በዚህ መልኩ መሰብሰቡ ደግሞ የመረጃ ድግግሞሽን በማስከተል መንግሥት ሥራ አፈፃፀሞችን መሠረት አድርጎ በሚያወጣቸው ዕቅዶች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን ሲያሳድሩ ቆይተዋል፡፡ ኮሚሽኑ ችግሩን መነሻ አድርጎ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት ፍኖተ ካርታ በአማካሪ ድርጅት አዘጋጅቷል፡፡
የሥራ ገበያ ስርዓት ውስጥ የሚገኙትን የመንግሥት፣ የግልና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተዋናዮችን በሙሉ ወጥና ተናባቢ በማድረግ ሥርዓቱን የማዋቀር ሥራ በፍኖተ ካርታው እንደተዳሰሰና ለዚህ መነሻው ደግሞ የጥናት ግኝቶች መሆናቸውን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡
ዳይሬክተሩ የመረጃ ድግግሞሽ፣ የተመሳሳይነትና ተነባቢነት ማጣት እንዲሁም አግባብነቱን የጠበቀ አለመሆን በሰፊው የተለዩ ችግሮች እንደነበሩም ተናግረዋል፡፡ከዚህ ቀደም የነበሩት የሀሰት ሪፖርት ችግሮች መንግሥት በሕዝብ ዘንድ ያለውን ተዓማኒነት በማሳጣት የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ሲያስነሱ ቆይተዋል፡፡በአገሪቱ ምን ያህል ሥራ ፈላጊ ዜጎች እንዳሉም ለማወቅ የመረጃ መፋለስ ይታያል ፡፡
ችግሮቹን ለማቃለል አሠራር መዘርጋት ቀዳሚው ተግባር በመሆኑ ፍኖተ ካርታው የሥራ ገበያው ተዋናይ የሆኑትን ባለድርሻ አካላት በማቀናጀት ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውን ዕውቀታቸውን እንዲሁም ቴክኖሎጂያቸውን በጋራ በመጠቀም ዘርፉን ማዘመን ላይ መሥራት እንዳለባቸው እንደሚያስቀምጥ የገለፁት ዳይሬክተሩ፤ በአዲሱ አሠራርም ከአንድ ቦታ የሚመነጨው መረጃ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ከወረዳ እስከ ላይኛው የፌዴራል መዋቅር ድረስ ተቀናጅቶ እንዲቀመር ያደርጋል ብለዋል፡፡
በአገር ደረጃ ከእያንዳንዱ የመኖሪያ ቤት የሚሰበሰቡት የሥራ ገበያ መረጃዎች ተናባቢ መሆናቸውና አግባብነታቸው ተረጋግጦ የተሟላ እንዲሆኑ በማድረግ ጥራቱን የጠበቀ የመረጃ ፍሰት እንደሚያሰፍንና ከዚህ ቀደም ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን እንደሚያቃልል ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡
ሥራውን ለሚሠሩ ከ 121 ወረዳዎች ለተውጣጡ የአንድ ማዕከል ሠራተኞችና በማዕከል ደረጃ ለአንድ የከተማ የቢሮ ኃላፊ ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን በተገኘ ድጋፍ በ 60 ሺህ የአሜሪካ ዶላር 122 ታብሌቶች የተሰራጩ ሲሆን፤ ሠራተኞቹ ወደ ሥራ ሲገቡም የመረጃ ሥርዓቱ የሥራ አፈፃፀም ሪፖርትን እንደሚያመነጭ ይጠበቃል፡፡
ቀደም ሲል ተመዝግበው የሥራ አጥ መታወቂያ ስለወሰዱ ብቻ ሳይደራጁ እንደተደራጁ ተደርጎ ይቀርቡ የነበሩትን የሀሰት መረጃዎችን እንዲሁም አለአግባብ ተጋንነው የሚቀርቡ የቁጥር ሪፖርቶችን ያስቀራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡
ዳይሬክተሩ፤ ሥራ ፈላጊዎች በቀላሉ ጉልበታቸውንና ጊዜያቸውን በቆጠበ መልኩ ከሥራ ጋር የሚገናኙበት ሥርዓት እንደሚፈጥርና በቀላሉ ጉግል ፕሌይ ስቶርን በመጠቀም ከሥራ ጋር የሚገናኙበትን ሁኔታ እንደሚያመቻች ገልፀዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱን ማግኘት የሚችሉት በጥቃቅንና አነስተኛ በአንድ ማዕከል የተደራጁት ብቻ ሲሆኑ፤ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ግን በአገሪቱ የሚገኙ ሁሉም ሥራ ፈላጊዎች አገልግሎቱን ማግኘት እንዲችሉ ይደረጋል፡፡
የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን ባደረገው ጥናት በከተሞች 19 ነጥብ አንድ በመቶ የሥራ አጥ ምጣኔ እንዳለ ያመላከተ ሲሆን፤ በሌላ በኩል በቅርቡ የተደረጉ ጥናቶች ደግሞ በየዓመቱ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሥራ ፈላጊዎች ወደ ገበያው እንደሚቀላቀሉ ያሳያሉ፡፡ በዚህ መነሻም በተያዘው በጀት ዓመት ለሦስት ሚሊዮን ሥራ ፈላጊ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዷል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 3/2012
ፍዮሪ ተወልደ