-ኢትዮጵያዊነትን ከማንነት ጋር አስተሳስሮ የሚያስኬድ ነው
-ራስን በራስ የማስተዳደር፣ ቋንቋን ወደ ፌዴራል የማሳደግ እድል ይፈጥራል
አዲስ አበባ:- የኢህአዴግ ውህደት ኢትዮጵያዊነትን ከማንነት ጋር አስተሳስሮ የሚያስኬድ፣ ራስን በራስ የማስተዳደርና ቋንቋን ወደ ፌዴራል የማሳደግ እድል የሚፈጥር የእውነተኛ ፌዴራሊዝም መተግበሪያ መሆኑን የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
በኢህአዴግ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪክ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ አሃዳዊ ስርዓት በኢትዮጵያ የሚታሰብ አይደለም። ይለቁንም የውህደት ጉዞው ኢትዮጵያዊነትን ከማንነት ጋር አስተሳስሮና አጣጥሞ የሚያስኬድ የእውነተኛ ፌዴራሊዝም መተግበሪያ ነው።
የኢህአዴግ መዋሀድ ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር፣ ቋንቋቸውን የመጠቀምና ብሎም ወደ ፌዴራል የማሳደግ እድል የሚሰጥ፤ የጋራ የሆነችውን ኢትዮጵያንም በባለቤትነት ስሜትና በእኩል ተሳትፎ ማልማትና መገንባት የሚችሉበትን እድል የሚሰጥ መሆኑን አቶ ፍቃዱ አብራርተዋል፡፡
የኢህአዴግ ውህደት በኢትዮጵያ የነበረውን ፍትሃዊ ተሳታፊነትና አካታችነት የጎደለው አካሄድን በመለወጥ በፓርቲው ውስጥ የነበሩ ችግሮችን የሚፈታና የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል እውነተኛ ፌዴራሊዝም የሚመሰረትበት ነውም ብለዋል።
ውህደቱ ሁሉም እኩል የሚሳተፍበትንና የሚወከልበትን እድል በመፍጠር አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ የመገንባት ሕገመንግሥታዊ አቅጣጫንምእውን ማድረግ ያስችላል ነው ያሉት አቶ ፍቃዱ፡፡
እንደ አቶ ፍቃዱ ገለጻ፤ የውህደት ጉዳይ ከአምስተኛው የኢህአዴግ የመደበኛ ጉባኤ ጀምሮ ሲነሳ የነበረ፤ በአስረኛው የመቀሌው ጉባኤ ላይ ውሳኔ የተላለፈበትና በ11ኛው ጉባኤ ጥናቱ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ተወስኖ ሂደቱ እንዲፋጠን ከማድረግ አኳያ ውክልና ለምክር ቤቱ የተሰጠበት ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ሲታይ ውህደቱ የዘገየ እንጂ ፈጠን የማይባል፤ የድርጅቱን ውሳኔ ከማስፈጸም አኳያም ሆነ የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል እርምጃ ለመውሰድ ቁርጠኛ አመራር መኖሩን የሚያመለክት ተግባር ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል፡፡
በመሆኑም የውህደት ጉዞው የተጀመረው ሁሉም በፍትህ የሚወከልበትና አካታች ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመፍጠር፤ ዛሬ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ሁኔታ ቀድሞ ኢህአዴግ በግንባር ሲደራጅ ከነበረው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ፈጽሞ የማይገናኝ በመሆኑ ወቅቱን ያማከለ አደረጃጀት መፍጠር በማስፈልጉ ነው፡፡ ውህደቱ እውን የሚሆንበት ጥናትም በየደረጃው ውይይት ተደርጎበታል፣ውህደቱም እስከ ምርጫ 2012 እውን ይሆናል፡፡ ለዚህም በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ሲሆን፤ የፓርቲው ማኑፌስቶም እየተዘጋጀ ይገኛል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 2/2012
ወንደሰን ሽመልስ