አዲስ አበባ፡- በአምቦና ጅማ ዩኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማሩ ሂደት ሰላማዊ ሆኖ እንዲቀጥል እየተሰራ መሆኑን የዩኒቨርሲቲዎቹ ፕሬዚዳንቶች ገለፁ፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከስሜታዊነት ወጥተው በትምህርታቸው ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርጉም አስገንዝበዋል፡፡
የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ታደሰ ቀነአ እና የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀማል አባፊጣ በየበኩላቸው በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፣ በዩኒቨርሲቲዎቹ የመማር ማስተማሩ ሂደት ሰላማዊ እንዲሆን ባለው መዋቅር መሰረት ከተማሪ ተወካዮች ጋር ውይይት እየተደረገ ነው፡፡የፀጥታ ዘርፉም ተጠናክሮ ሥራውን እየሰራ ይገኛል፡፡በዩኒቨርሲቲዎቹ ከሚመደቡ የፀጥታ አካላት፣ከአካባቢው መስተዳድር፣ከየዩኒቨርሲቲዎቹ ቦርድ እንዲሁም አስተዳደሮች ጋር በመሆንም በየጊዜው በመገናኘት እየተሰራ ነው፡፡
ዶክተር ታደሰ እንደገለጹት፣ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማሩ ሥራ ሰላማዊ በሆነ መልኩ እየተካሄደ ነው፡፡በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሲቲው ምንም አይነት ችግር የለም፡፡ችግር እንዳይከሰት በሚልም ተማሪዎችን የማረጋጋት ሥራ እየተሰራ ነው፡፡ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
‹‹በአንድ ቦታ ችግር ሊከሰት ይችላል፤ ይህን ችግር መፍታት እንጂ ወደሌላ አካባቢ ማዛመት የሚያስገኘው ጥቅም የለም፡፡››ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣‹‹ወንጀል የሰራ ግለሰብ ተፈልጎ በወንጀሉ ይጠየቃል እንጂ ሌላ ወንጀል በሌላ ቦታ የሚሰራበት ምንም ምክንያት አይኖርም›› ብለዋል፡፡
‹‹ወንጀል ብሄርም ቋንቋም የለውም፣የትም ቦታ ወንጀል የሰራ ግለሰብ ለሰራው ወንጀል መጠየቅ አለበት፣ሌላ ቦታ የተሰራን ወንጀል ማስፋፋት ትርፉ አገሪቱን በማፍረስ ራስን መልሶ መጉዳት ነው›› ያሉት ዶክተር ታደሰ፣ሁሉም ሰው በሰከነ አእምሮ መንቀሳቀስ እንዳለበት አስታውቀዋል፡፡
ያጠፋውን ግለሰብ መሰረት ያደረገ ህጋዊ ርምጃ መንግሥት እስኪወስድ በትዕግስት መጠበቅ እንደሚገባም አስገንዝበው፣ ከስሜታዊነትም በመታ ቀብ በየአካባቢው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲቀጥል ሁሉም የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀማል በበኩላቸው፣ተማሪዎች ጥያቄ ቢኖራቸው እንኳ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማቅረብ እንደሚችሉ አስታውቀዋል፡፡ በአንድ ቦታ የሚፈጠር ችግር ወደሌላው ቦታ እንዳይዛመት መንግሥትም ቁርጥ ያለ አሰራር ማስቀመጥ እንደሚጠበቅበትም አመልክተዋል፡፡
መንግሥት የደረሰበት መረጃም ካለ ለተማሪም ሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብ ወዲያው ማሳ ወቅ እንደሚኖርበትም አስታውቀው፣ይህ ካልሆነ በየዩኒቨርሲቲዎቹ ላይ ጫና እንደሚፈጠር እና በአጥፊው ላይ እየተወሰደ ያለውን ርምጃም መግለፁ ተገቢ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡በዚህም ተማሪዎችም ሆኑ የተቀረው ህዝብ እንደሚረጋጋም ገልጸዋል፡፡
ተማሪዎች ከስሜታዊነት ተጠብቀው በተረጋጋ መንፈስ ለትምህርታቸው ትኩረት መስጠት እንደሚጠበቅባቸው ዶክተር ጀማል አስገንዝበው፣ ስሜታዊ በመሆን ያልተገባ ርምጃ መውሰድ የበለጠ አደጋ እንደሚያመጣም አመልክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 2/2012
አስቴር ኤልያስ