• ህብረተሰቡ ችግኞችን እንዲንከባከብም ጥሪ ቀርቧል
አዲስ አበባ:- በአዲስ አበባ ከተማ ህገ-ወጥ የመሬት ወረራና የሕንፃ ግንባታዎች ለአረንጓዴ ልማት ዘርፉ እንቅፋት መሆኑ ተገለጸ። ህብረተሰቡ የተከላቸውን ችግኞች እንዲንከባከብም ጥሪ ቀርቧል::
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተፋሰስና አረንጓዴ አካባቢዎች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወሰን መግራ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት በከተማዋ ከሚገኙ ክፍለ ከተሞች ስድስቱ ተለይተው የከተማ የደን ልማት እየተካሄደ ሲሆን እስከ ወረዳ ድረስ መዋቅር ተዘርግቶ የማልማት፣ የመንከባከብና የመጠበቅ ሥራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ።
በተለይ ባለፈው ክረምት በአገር አቀፍ ደረጃ የተያዘውን የአረንጓዴ ልማት ሥራ ተከትሎ በከተማዋ ከፍተኛ የችግኝ ተከላ መካሄዱን የጠቆሙት አቶ ወሰን ሆኖም የአረንጓዴ ልማት ሥራው የተለያዩ ችግሮች እየገጠሙት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
በተለይ ለአረንጓዴ ስፍራነት የተለዩ ቦታዎችን ለግል ጥቅም ሲባል መግፋትና ማጥበብ፣ አንዳንዴም ጭራሹን መጠቅለልና ለግንባታ ማዋል፣ ሕንፃ ሲሠራ ከተማዋን የለመዱና የአየር ንብረቱን የተዋሃዱ ዛፎችን በዲዛይን ማዳን እየተቻለ መቁረጥ፣ ህግ-ወጥ የመሬት ወረራና የግንዛቤ ማነስ የአረንጓዴና ደን ልማቱን ከማሳካት አኳያ የሚያጋጥሙ እንቅፋቶች መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
የተተከሉ ችግኞች እንክብካቤና አያያዝን በተመለከተ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንደጠቆሙት እስከ መስከረም መጨረሻ ድረስ ዝናብ ያለ ማቋረጥ ሲዘንብ በመቆየቱ ውሃ ማጠጣቱ አስፈላጊ አልነበረም። ከአሁን በኋላ ግን የመንከባከቡን ተግባር በተጠናከረ መልኩ ማከናወን ተገቢ ነው፡፡
በዚህም መነሻነት ችግኞችን ለመንከባከብ በየክፍለ ከተማው ሁለት ሁለት የውሃ ማመላለሻና ማጠጫ ቦቴዎች መመደባቸውንና በዘርፉ በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ ወጣቶችም ሥራውን በቋሚነት ለመሥራት ወደ ሥራ መግባታቸውን አቶ ወሰን ተናግረዋል፡፡
ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ለመከላከል አጥር የማጠር ሥራዎችም እየተሠሩ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ወሰን በመሆኑም ከመትከል እስከ ፅድቀት፣ ጥበቃና እንክብካቤ ድረስ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ እንደሚሠራ ተናግረዋል::
ሥራውን ኤጀንሲው በበላይነት ቢያስተባ ብርም ችግኞችን የመንከባከቡና የመጠበቁ ድርሻ ግን የመላ ከተማዋ ነዋሪዎች በመሆኑ እከሌ ከእከሌ ሳይባል ሁሉም የከተማዋ ነዋሪ ያለማቋረጥ በአረንጓዴ ልማቱ ላይ በዘላቂነት መሳተፍ አለበት ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
አቶ ወሰን እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ የመንከባከቡን ሥራ እራሳቸው መጀመራቸው ለመላው የአገሪቱ ህዝብ መልካም ምሳሌ ነው፤ ሁሉም የከተማዋ ነዋሪም ይህንን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ተግባር በአርኣያነት በመውሰድ የየራሱን ድርሻ ሊወጣ ይገባል፡፡
“የሙቀት መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄድ፣ የከተሜነት መስፋፋት፣ መሰረተ ልማት ግንባታ በስፋት መከናወን ወዘተ የሚገኝበት ወቅት ላይ ነው የምንገኘው፤” የሚሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ለዚህ ችግር መፍትሔ የሚሆነው ደግሞ ችግኞችን የመትከል፣ ያሉትንም የመንከባከብና ሌሎች ተያያዥ ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል ነው ብለዋል፡፡
“መትከል አንድ ቀን ነው፤ መከላከል ግን ዘላቂና የሁል ጊዜ ሥራ ነው” የሚሉት አቶ ወሰን ከተማዋ እራሷን በልታ ጭራሹን እንዳትጠፋ፣ ለኑሮ ምቹ እንድትሆን ማድረግ፣ በረሀማነትን መከላከል፣ ለአረንጓዴ ስፍራነት የተተዉ ቦታዎችን የማልማትና የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችል አቅም የመፍጠር ኃላፊነት በሁላችንም ላይ የወደቀ በመሆኑ ሁላችንም የተከልነውንም ሆነ ያልተከልነውን ችግኝ መንከባከብ ይጠበቅብናል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 1/2012
ግርማ መንግሥቴ