አዲስ አበባ፡- በመንግሥት ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ቁጥር መብዛቱን ተከትሎ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችን እያስገነባ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ አስታወቀ። በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች በክፍል ውስጥ ያለው የተማሪ ጥምርታ ከእስታንዳርድ በላይ ነው።
የቢሮው የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ አበባ ቸርነት በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት በ2012 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ላይ የተማሪዎች ቁጥር ከተለመደው በላይ ጨምሯል። የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ምቹ መሆን በተቃራኒው የግል ትምህርት ቤቶች የክፍያ ዋጋ መወደድ ጋር ተከትሎ በርካታ የግል ትምህርት ቤት ተማሪዎች ወደ መንግሥት ትምህርት ቤት እንዲያማትሩ አድርጓቸዋል።
መንግሥትም ይህን ችግር በመገንዘብ በጊዜያዊነት ችግሩን ለመፍታት በርካታ ትምህርት ቤቶች በፈረቃ እንዲያስተምሩና ተማሪዎች ያለችግር መማር እንዲችሉ እየሠራ ነው። በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች አሁን ያለው ጥምርታ በክፍል እስከ 90 ተማሪዎች መድረሱን ጠቅሰው በእስታንዳርዱ መሰረት ግን እስከ 50 ተማሪ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።
መንግሥት የትምህርት ተደራሽነትን እያስፋፋና በትምህርት ስርዓቱ ላይ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን እየቀረፈ መሆኑን የተናገሩት አቶ አበበ ይህን ተከትሎ በርካታ ተማሪዎች ወደ መንግሥት የትምህርት ተቋም ይመጣሉ ተብሎ ይታሰባል። በመሆኑም ሊያጋጥም የሚችለውን የክፍል ጥበት በዘላቂነት ለመፍታት ትምህርት ቢሮው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በርካት ትምህርት ቤቶችን እያስገነባ ነው።
በአዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢዎች የትምህርት ስርዓቱ ከሚፈቅደው በላይ እስከ ዘጠና የሚደርሱ ተማሪዎች በአንድ ክፍል ውስጥ እየተማሩ ነው። ይህን ችግር በአፋጣኝ ለመፍታትና በትምህርት ስርዓቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳያሳድር በነባር ትምህርት ቤቶች ውስጥ የማስፋፊያ ግንባታዎች በፍጥነት እየተገነቡ ነው። አንዳንድ ትምህርት ቤቶች የማስፋፊያ ሥራቸውን ጨርሰው ወደ ሥራ ገብተዋል ያሉት ኃላፊው በቀጣይም በርካታ አዳዲስ ትምህርት ቤቶችና ማስፋፊያዎች ወደ ሥራ እንደሚገቡ ገልጸዋል።
የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊው አክለው እንዳብራሩት የተማሪ ቅበላ የበዛባቸው ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን በፈረቃ ለማስተማርና ሙሉ ጊዜ ከሚማሩ ተማሪዎች ጋር እኩልና ፍትሐዊ የሆነ የመማር ማስተማር ስርዓት እንዲኖር ለማድረግ ብቁ የሆነ የሰው ኃይል ለማሟላት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው። በፈረቃ በሚማሩ ተማሪዎች ላይ ምንም ዓይነት የትምህርት አሰጣጥ ችግር አይኖርም። ፈረቃውን የሚመጥን የትምህርት ክፍለ ጊዜ ወጥቶ ተግባራዊ ሆኗል። መሸፈን ያለባቸው ትምህርቶች በክፍለ ጊዜው መሰረት ስለሚሰጡ የተለየ ችግር እንደማይኖር አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 30/2012
ሞገስ ፀጋዬ