አዲስ አበባ፡- በሀገር አቀፍ ደረጃ የአካል ጉዳተኞችን ሰብዓዊ መብት የሚያስከብር ወጥ የህግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ አካል ጉዳተኞች ለተለያዩ ችግሮች እየተጋለጡ መሆናቸውን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ።
የፍርድቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንትና የሬጅስትራር ተወካይ አቶ ሀብቴ ፍቻላ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ አካል ጉዳተኞችን በሚመለከት ያሉት ህጎች ወጥ ባለመሆናቸውና የሚገኙትም በተለያዩ ሰነዶች ተበታትነው በመሆኑ አካል ጉዳተኞች ህጎችን አውቀው የመብታቸው ተጠቃሚ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል።
ወጥ የሆነ ህግ አለመኖሩ ጠበቆችም ሆኑ ዳኞች ብዙ ነገሮችን አገላብጠው እንዲሠሩ እየተገደዱ መሆናቸውን የሚያነሱት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ አሁን ባለው የውስጥ አሠራር ስርዓት የተለያዩ ማጣቀሻዎችን በማስገባት የተለያዩ ጉዳዮች የሚታዩ መሆኑን ገልጸዋል። ይሄ ደግሞ እያንዳንዱ ሰብዓዊ መብታቸው ተካቶ እንዳይሠራ ይገድባል። በመሆኑም አሁን ሁሉንም አካታች በሆነ መልኩ ለመሥራት የሚያስችል የህግ ማዕቀፉ እየተከለሰ መሆኑን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህርና ጠበቃ ረዳት ፕሮፌሰር አስቻለው አሻግሬ በበኩላቸው፤ በተለያየ መንገድ የአካል ጉዳተኞችን ሰብዓዊ መብት የሚያስጠብቁ ህጎች እንዳሉ አንስተው፤ ወጥ ሆነው ባለመቀመጣቸው የችግር ተጋላጭነታቸውን አወሳስቦታል ብለዋል።
“ዳኞች ስለ አካል ጉዳተኞች የወጡ ህጎችን በሙሉ ማወቅ አይችሉም።” ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ ይህ ባልተሟላበት ሁኔታ መብታቸው ሳይከበር ፍርድ ሊሰጥ እንደሚችል ጠቅሰዋል። በተመሳሳይ አቃቢ ህግም ሆነ ባለጉዳዩ ምን ድረስ መብት እንዳለው እንዳይረዳ ሆኗል። ይህ ደግሞ በሰብዓዊ መብቱ ዙሪያ እኩል ተጠቃሚ እንዳይሆኑ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
ረዳት ፕሮፌሰሩ እንዳሉት፤ ወጥ የሆነ የህግ ማዕቀፍ መኖር ወጥና ህጉን መሰረት ያደረገ ፍርድ እንዲሰጥ ያደርጋል፤ በተበታተነ መልኩ ያለውን የአካል ጉዳተኞችን መብትና ህግጋት በሚገባ ለመተግበር ያስችላል። ህጉ ተደራሽ ሆኖ ዳኛው፣ አቃቢ ህጉ፣ ባለቤቱና ማህበረሰቡም በአግባቡ እንዲረዳውና ለአካል ጉዳተኞቹ መብት ጥበቃ እንዲያውለውም ያግዛል። ሆኖም አሁን ያለው ሁኔታ ይህ በተግባር እየዋለ ስላልሆነ የአካል ጉዳተኞች ሰብዓዊ መብት ጥበቃ ድምፅ አልባ እንዲሆን ማድረጉን ተናግረዋል።
መንግሥት ለጉዳይ ትኩረት አልሰጠም፤ ለችግር ተጋላጭነታቸውን ቢያምንም በተግባር ሰብዓዊ መብታቸውን ማስጠበቅ ላይ ግን ይቀረዋል የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ የአካል ጉዳተኞች ሰብዓዊ መብት ከጊዜ ወደጊዜ እየተጣሰ ስለሆነ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባና ስምምነት ከመፈረም ባሻገር ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 30/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው