ኢትዮጵያ በዓለም ቀደምት የሆኑትን የአይሁድ፣ የክርስትናንና የእስልምናንና ሃይማኖቶች በፍቅር ተቀብላ ለዘመናት በመፈቃቀርና በመከባበር እንዲኖሩ ያደረገች ሀገር ነች፡፡ ኢትዮጵያ የፍትሐዊነትና የእንግዳ ተቀባይነት ተምሳሌት በመሆኗም ነብዩ ሞሃመድ ተከታዮችቸውን ወደዚቹ የተመረጠች ሀገር እንዲሄዱ አዘዋል፡፡ በተለያዩ የሃይማኖት ቅዱስ መጽሐፍትም በጎ ስሟ ተደጋግሞ ተነስቷል፡፡
ከሃይማኖቶችና እምነቶች ባሻገርም ኢትዮጵያ በርካታ ባህሎች የሚንጸበረቁባትና የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች በጋራ የሚኖሩባት ህብረብሄራዊ አገር ናት፡፡ እነዚህ የተለያዩ ማንነቶችና ባህሎች ግን በህዝቦች አንድነትና አብሮ መኖር ላይ ምንም ዓይነት እንቅፋት ሲፈጥሩ አልታዩም፡፡ በልዩነቶች ውስጥ የሚታዩት ጠንካራ የመከባበርና የመቻቻል ባህሎች ዜጎች ያለምንም ኮሽታ በፍቅር አብረው እንዲኖሩ አስችሏቸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የተለያዩ አብነቶችን ማንሳት ይቻላል፡፡
በኢትዮጵያ ማህበረሰብን ለማስቀጠል ትልቅ ሚና ባላቸው ከጋብቻ እስከ ጉርብትና ድረስ አንዱ ከሌላው ጋር ተዋህዷል፤ ተጋምዷል፡፡ ከተለያዩ ብሄረሰቦችና እምነቶች የተገኙ ጥንዶች ትዳር መስርተው በፍቅር የሚኖሩበትን ነባራዊ ሁኔታ መመልከትም እንግዳ አይደለም፡፡ ከዚህም ባሻገር በሁሉም አካባቢ ያለው ኢትዮጵያዊ እርስ በርሱ ያለ ው የጉርብትናና የዝምድና መስተጋብር ፍፁም የተዋሃደ ነው፡፡
በአገራችን ጉርብትና ሲመሰረት ዘርን፣ ሃይማኖትን ወይም ሌላ ቅርበትን መነሻ በማድረግ አይደለም። አጋጣሚዎች የሚያገናኟቸው ኢትዮጵያውን ጎረቤት ሲሆኑ ለዘመናት የቆየው የአብሮነት ባህሉ በመካከላቸው ገብቶ አንድነታቸውን ያጠናክረዋል፡፡ “ከሩቅ ዘመድ የቅርብ ጎረቤት ይሻላል” የሚለው የኢትዮጵያውያን አባባልም ከዘርና ከዝምድና ይልቅ አብሮ መኖር ትልቅ ቦታ እንዳለው የሚያመላክት ነው፡፡
በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ጉርብትና ትልቅ ቦታ አለው፡፡ አብሮ ከመብላትና ከመጠጣትም ባሻገር ጎረቤት ገመና ከታች እንደሆነ ይነገራል፡፡ በችግርም ሆነ በደስታ ወቅት ቀድሞ ደራሽ ጎረቤት በመሆኑ የጎረቤት ማህበራዊ መስተጋብር ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡ ከዚህ ከፍ ሲልም በአንድ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች የዘርና የሃይማኖት ልዩነቶች ሳይገድባቸው የሚተሳሰሩባቸውን ማህበራዊ ተቋማት ይገነባሉ፡፡
ከእነዚህም ውስጥ እድር፣ እቁብ፣ ደቦ፣ ወዘተ ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ ማህበራዊ ተቋማት ማህበረሰቡ የተለያዩ የህይወት ፈተናዎች ሲያጋጥመው ችግሮቹን የሚፈታበት ወይም በደስታ ጊዜ አብሮ የሚያሳልፍባቸው ናቸው፡፡ በዚህ የተነሳ በአገራችን ማህበራዊ ህይወት ከሃይማኖትም ሆነ ከብሄር በላይ ትልቅ ፋይዳ ያለው የትስስር ገመድ ሆኖ አገራዊ አንድነትን አጠናክሮ ኖሯል፡፡
ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ የአገራችን ክፍሎች የተከሰቱ ግጭቶች እነዚህን ማህበራዊ መሰረቶች የሚንዱና የቆየውን የአገራችንን ብሄር ብሄረሰቦች አብሮ የመኖር ባህል የሚጥስ ድርጊት ነው። በተለይ ለዓመታት አብረው የኖሩና በተለያዩ መንገዶች ትስስራቸው ውህደት ፈጥሮ አንዱን ከሌላው መለየት በማይቻልበት የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ብሄርና ሃይማኖት እየለዩ የሚደረጉ ግጭቶችና የማፈናቀል ድርጊት የአገራችን ባህል አይደለም፡፡
በርግጥ እንዲህ ዓይነት ግጭቶች በህዝቡ ፍላጎት የተከሰቱ እንዳልሆኑ የተለያዩ ማሳያዎች አሉ፡፡ ለዚህም ከግጭቱ በኋላ በተለያዩ አካባቢዎች በሚደረጉ ህዝባዊ ውይይቶች ላይ ህብረተሰቡ የሚያነሳቸው ሃሳቦች ማሳያ ናቸው፡፡ በውይይት መድረኮቹ ላይ ህዝቡ ግጭቶቹ ከሱ እውቅና ውጪ የተፈፀሙ መሆናቸውን ደጋግሞ ያነሳል፡፡ በቅርቡ በተለያዩ አካባቢዎች በተደረጉ የእርቅ ስነስርዓቶችም ላይ በተፈጠሩ ችግሮች የተሰማውን ኀዘኔታ በእምባ ጭምር ሲገልጽ ተስተውሏል፡፡
በመሆኑም እንዲህ ዓይነት ህዝብን የሚከፋፍሉና በየጊዜው ለሞትና መፈናቀል የሚዳርጉ ተግባራትን መዋጋት ከእያንዳንዱ ህብረተሰብ ይጠበቃል፡፡ በተለይ በየጊዜው በህዝቡ መካከል እየገቡና ህዝብና ህዝብን እያላተሙ ደም ካፈሰሱ በኋላ ዞር የሚሉ አካላትን ነቅቶ መጠበቅና ሰላምን ማስጠበቅ የእያዳንዱ ዜጋ ኀላፊነት ሊሆን ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 29/2012