በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የተመራው የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ጋባዥነት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሲያካሂድ የነበረውን ውይይት አጠናቋል።
የውይይቱን መጠናቀቅ አስመልክተው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ ዶክተር ስለሺ በቀለ እና አምባሳደር ፍፁም አረጋ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል::
በመግለጫቸውም ኢትዮጵያ በናይል ወንዝ ላይ ፍትሐዊና ሚዛናዊ የውሃ መብት እንዳላትም ማስገንዘቧን ነው ያስታወቁት።
ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል የማያገኝ 70 ሚሊየን ህዝቧ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ ለማድረግ እና ለድህነት ቅነሳ ጥረቷ እንጂ ማንንም አካል የመጉዳት አላማ እንደሌላት አስታውቃለች ብለዋል።
እንዲሁም ለሦስትዮሽ ውይይቱ አሁንም ትልቅ ግምት እንደምትሰጥ እና በግድቡ ዙሪያ ያሉ ማናቸውም አለመግባባቶች በቴክኒክ ባለሙያዎች ሙያዊ ምክክር ብቻ እንደሚፈቱ እንደምታምን አስረድታለች።
በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ የነበሩ ብዥታዎችን ግልፅ ለማድረግና የኢትዮጵያ አቋም ገንቢ መሆኑን ለማስረዳትም የምክክር መድረኩ ጠቃሚ እንደነበር በመግለጫው ተገልጿል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ በቦታው በመገኘት ሪቫን አብረው በመቁረጥ ለመመረቅ ፍላጎት እንዳላቸው መግለፃቸውን በመግለጫው ላይ ተጠቁሟል::
በተደረገው ውይይት መሰረትም የሦስቱ አገራት ሚኒስትሮች በታላቁ የህዳሴ ግድብ አሞላል ዙሪያ ገንቢ፣ ቀጣይነት ያለውና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ስምምነት ላይ ለመድረስ ተስማምተዋል። መረጃውን ያገኘነው በአሜሪካ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ነው።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 29/2012