የነብዩ ሙሐመድ የልደት በዓል ከሳኡዲ ዓረብያ በስተቀር በሁሉም የዓለም አገራት በድምቀት ይከበራል። ኃይማኖታዊ ገጽታውን ሳይለቅ የየሀገሩን ታሪክና ባህል መሰረት አድርጎ በሁሉም የዓለም ጫፍ በድምቀት ይከበራል።
አውስትራሊያ
በአውስትራሊያ የመውሊድ በዓል ቀኑን ሙሉ ይከበራል። በዕለቱ የእምነቱ ተከታዮች ይሰባሰባሉ። ስለነብዩ ሙሐመድ መንፈሳዊ ትምህርቶች ይነገራሉ። አንዳንድ ሙስሊሞች ደግሞ ለልጆች ብቻ ክፍል አዘጋጅተው መንፈሳዊ ትምህርት ይሰጧቸዋል። በክፍሉ ውስጥም የተለያዩ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን ይቀስማሉ። ክፍሉም የነብዩ ሙሐመድን ልደት በሚያንፀባርቁ ልዩ ልዩ ጌጣጌጦችና አልባሳት ያሸበርቃል። መጽሐፎች ይነበባሉ፤ ስለነብዩ ሙሐመድ እና ስለ እስልምና ሕይወት በሰፊው ይሰበካል።
ፓኪስታን
በመውሊድ ቀን ሙሉ በሙሉ ሥራ የለም፤ ተቋማት ዝግ ናቸው፤ የንግድ ቤቶችም ዝግ ይሆናሉ። በዕለቱ ብዙ ሰዎች የበጎ አድራጎት ስጦታዎችን ያበረክታሉ። ስጦታዎች የሚበረከቱት ለተቸገሩ ወገኖች እንጂ የቅንጦት ስጦታ አይደለም። አሳዳጊ፣ ጧሪ እና ቀባሪ ለሌላቸው ተለይቶ ነው የሚሰጠው።
እነዚህ የበጎ አድራጎት ነገሮች በሁሉም አገራት የእስልምና እምነት ተከታዮች የሚከናወኑ ቢሆኑም የፓኪስታንን ለየት የሚያደርገው በዕለቱ የንግድ ተቋማት ሁሉ ዝግ ሆነው በመዋላቸው ነው። ባለሥልጣናት ሁሉ የሚሄዱት በህዝብ ትራንስፖርት ነው።
ሕንድ
ሌሊት ረጅም ፀሎት ይደረጋል፣ ሰልፎች እና የተለያዩ ትዕይንቶች ይደረጋሉ፤ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ ያከብራል። ሕንፃዎች፣ መስጊዶችና አደባባዮች በተለያዩ ባነሮች ያሸበርቃሉ። ስለነብዩ ሙሐመድ የተለያዩ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ይቀርባሉ።
በመውሊድ ዕለት በህንድ አረንጓዴ ባንዲራ ይያዛል፤ አረንጓዴ ባነሮች ይሰቀላሉ። አረንጓዴ የተመረጠበት ምክንያትም እስልምናን እና ጀነትን ይወክላል ተብሎ ስለሚታሰብ ነው።
እንግሊዝ
የነብዩ ሙሐመድ የልደት በዓል (መውሊድ) በእንግሊዝም የሚከበረው በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ነው። የሃይማኖት አባቶች ያስተምራሉ፣ የተለያዩ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ይቀርባሉ፤ መንዙማና ሌሎች ዜማዎችም ይዜማሉ። ሙስሊም ወላጆች ስለነብዩ ሙሐመድ ሥራዎች በስፋት ለልጆቻቸው ያ ስተምራሉ።
በእንግሊዝ 2 ነጥብ 8 ሚሊየን ሙስሊሞች ይኖራሉ ። በእንግሊዝ ውስጥ ከክርስትና ሃይማኖት ቀጥሎ ብዙ አማኝ ያለው እስልምና ነው። አብዛኛው ሙስሊም ማህበረሰብም የሚገኘው ለንደን ውስጥ ነው።
ግብጽ
መውሊድ በግብጽ በደመቀ ሁኔታ ይከበራል። እንደ ከረሜላ ያሉ ጣፋጭ ነገሮችና አሻንጉሊቶች ይገዛሉ፤ ለሴት ሙሽሮችና ለፈረስ ጋላቢ ወንዶች ይበረከታሉ። አሻንጉሊቶቹ በተለያዩ ጌጣጌጦች ያሸበርቃሉ። ጎረቤቱና አካባቢውም በሰው ብዛት ይጨናነቃል። በተለያዩ ሃይማኖታዊ ዝግጅቶች ይከበራል።
አባቶች ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን ይሰጣሉ፤ ልጆች ስጦታ ይሰጣጣሉ።
ጣሊያን
ጣሊያኖች የበዓሉ ዕለት ጠዋት ወደ መስጊድ ይሄዳሉ። ከመስጊድ በኋላ ቤተሰብ ይሰባሰብና በድምቀት ይከበራል። በዓሉ የሚከበረው ከጎረቤት ጋር በጋራ ነው። አከባበሩም ከአብዛኞቹ የሰሜን አፍሪካ አገራት ጋር ይመሳሰላል። ለልጆች ልብስ ይገዛል፤ ዘመድ አዝማድ ይጠያየቃል። ኬክ በልዩ
ሁኔታ ይዘጋጃል።
ጀርመን
የመውሊድን በዓል በጀርመን የተለያየ እምነት ተከታዮች አብረው ሆነው ያከብሩታል። በአደባባይ ወጥተውም ስለአብሮ መኖርና መቻቻል ይማማራሉ። ታላላቅ ባለሥልጣናትም ይገኛሉ፤ ንግግርም ያደርጋሉ። ፕሮግራሙ በቅዱስ ቁርዓን ንባብ ይጀመራል። ወጣቶችም በተለያዩ ቋንቋዎች ትዕይንቶችን ያቀርባሉ።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 29/2012
ዋለልኝ አየለ