– ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ዓረብኛ ቋንቋን ይሰጣል
አዲስ አበባ:- በሱዳን ካርቱም የሚገኝው ኢንተርናሽናል ዩኒቨርሲቲ ኦፍ አፍሪካ በአማርኛና በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ በዲግሪ ደረጃ ለማስተማር ስምምነት ላይ መድረሱ ተገለፀ። ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲም ዓረብኛ ቋንቋን በዲግሪ ደረጃ ሊሰጥ ነው።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሂዩማኒቲስ ቋንቋዎች ጥናት ጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ኮሌጅ ዲን ዶክተር አማኑኤል አለማየሁ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በተገባደደው በጀት ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ፣ ከኮተቤ ሜትሮፖሊታን እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጣ አንድ ልዑክ ቡድን ወደ ሱዳን አቅንቷል።
ልዑኩ ከሱዳኑ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች ጋር ባደረገው ውይይት የአማርኛና የአፋን ኦሮሞ ቋንቋዎችን በሱዳን ዩኒቨርሲቲ እንዲሰጥና የዓረብኛ ቋንቋን ደግሞ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተጨማሪ በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ እንዲሰጥ የሁለትዮሽ ስምምነት ላይ ተደርሷል።
እንደ ዶክተር አማኑኤል ማብራሪያ፤ የሱዳኑ ኢንተርናሽናል ዩኒቨርሲቲ ኦፍ አፍሪካ ቀደም ብሎ ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ እና ከኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ሲሰራ የነበረ ሲሆን በሱዳን በነበረው ውይይት ትብብራቸውን ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዲግሪ ደረጃ እየተሰጠ ያለውን የዓረብኛ ቋንቋን ከማጠናከር ባሻገር የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የዓረብኛ ቋንቋ ትምህርትን እንዲሰጥ ጥያቄ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያው ልዑክ ደግሞ የሁለቱ አገር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና የጋራ ታሪክ ይበልጥ እንዲጠናከር የዓረብኛ ቋንቋ በኢትዮጵያ ከመሰጠቱ በተጨማሪ የተለያዩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በሱዳን እንዲሰጡ ጥያቄ አቅርቧል። በዚህም አማርኛና አፋን ኦሮሞ በሱዳን እንዲሰጡና የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የዓረብኛ ቋንቋን ለመስጠት የሁለትዮሽ ስምምነት ላይ በመድረስ በጋራ ለመሥራት ተፈራርመዋል።
ቀደም ሲል ካርቱም ዩኒቨርሲቲ ውስጥ አማርኛ ቋንቋ ትምህርት ይሰጥ እንደነበር ያወሱት ዶክተር አማኑኤል፤ የሱዳኑ ኢንተርናሽናል ዩኒቨርሲቲ ኦፍ አፍሪካ ዓለም ዓቀፍ ዩኒቨርሲቲ በመሆኑ ከአፍሪካና ከተለያዩ የዓለም አገራት የተውጣጡ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በዚህ ዩኒቨርሲቲ ይከታተላሉ። እነዚህ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በዚህ ዩኒቨርሲቲ መሰጠቱ ለቋንቋዎቹ ዕድገት ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።
ስምምነቱን በቅርብ ጊዜ ወደ ተግባር ለማስገባት በዩኒቨርሲቲዎቹ ደረጃ አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር አማኑኤል፤ የቅድመ ዝግጅት ሥራው ሲጠናቀቅ በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች በኩል አስተማሪዎችን በመመደብና አስፈላጊ የሆኑ የትምህርት መርጃ መሣሪያዎችን ድጋፍ ያደርጋሉ።
እንዲሁም በሱዳኑ ዩኒቨርሲቲ በኩል ደግሞ የመምህራንን ወጪ ሙሉ ለሙሉ ከመሸፈን ባሻገር የበቁ የዓረብኛ ቋንቋ መምህራኖችን ሙሉ ወጪያቸውን ሸፍነው ወደ ኢትዮጵያ እንደሚልኩ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ዓረብኛ ቋንቋን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚማሩ ተማሪዎች ከክፍል ከወጡ በኋላ ቋንቋውን በማህበራዊ ህይወት እና በየዕለት እንቅስቃሴያቸው የሚያዳብሩበት ምቹ ሁኔታ እንደሌለ የሚናገሩት ዶክተር አማኑኤል፤ ተማሪዎች የመናገር ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ ዘንድሮ የዓረብኛ ቋንቋ ተመራቂ የሆኑ 30 ተማሪዎች ወደ ካርቱም አቅንተው በዩኒቨርሲቲው ልምምድ እንዲያደርጉ መፈቀዱን ገልፀዋል።
በኢትዮጵያና በሱዳንን እንዲሁም በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ቅርንጫፍ ያለው የሳዑዲ አረቢያው አልመቱም ፋውንዴሽን የተሰኝው ድርጅት ዩኒቨርሲቲዎቹ የደረሱበት ስምምነት ወደ ሥራ ሲገባ አስፈላጊውን የፋይናንስ ወጪ እንደሚሸፍን ታውቋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 29/2012
ሶሎሞን በየነ