– ለአንድ ኃላፊ የግል ችግር ዕርዳታ በሚል 125 ሺህ ብር ተሰጥቷል
– ከደንብና መመሪያ ውጭ ከ532 ሺህ ብር በላይ አበልና ደመወዝ ተከፍሏል
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር በሚገኙ ተቋማት ከግዥ አዋጅ መመሪያ ውጭ የተፈፀመ ከ529 ሚሊየን ብር በላይ ክፍያ መኖሩን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት አስታውቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ባቀረበው የኦዲት ሪፖርት መሰረት፤ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ በ27 ተቋማት ላይ በተደረገ የኦዲት ምርመራ 529 ሚሊየን 105 ሺህ ብር ከግዥ አዋጅ መመሪያ ውጭ ክፍያ መፈፀሙ ተረጋግጧል። በተለይ የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ትልቁን ድርሻ በመያዝ የ467 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ከመመሪያ ውጭ ክፍያ የፈፀመ ተቋም ሆኗል። የትራንስፖርት ባለሥልጣን እና መንገዶች ባለሥልጣን በ2010 ዓ.ም በድምሩ ከ40 ሚሊየን ብር በላይ ከአዋጅ ውጭ ክፍያ መፈፀማቸው በሪፖርቱ ቀርቧል።
እንደ ኦዲት መስሪያ ቤቱ መረጃ ከሆነ፤ በተለያዩ የአዲስ አበባ ተቋማት ውስጥ የወጪ አጠቃቀም ላይ የመንግፅት ግዥ አዋጆችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎች በአግባቡ አይከበሩም። የተሰብሳቢና ተከፋይ ሒሳቦችም በወቅቱ ሳይወራረዱ ይከማቻሉ።
በጉለሌ ክፍለ ከተማ ጽሕፈት ቤት ለአንድ ሃላፊ የግል ችግር ገጥሟቸዋል በሚል 125 ሺህ ብር ዕርዳታ እንዲደረግላቸው በካቢኔ ተወስኖ ከመንግሥት በጀት አሠራር ውጭ ክፍያ መፈፀሙ በኦዲት ተደርሶበታል። የኦዲት መስሪያ ቤቱም ለመንግሥት ሥራ ብቻ መዋል የነበረበት ክፍያ ወደግለሰብ መሄዱ አግባብ እንዳልሆነ በመግለጽ ተመላሽ እንዲደረግ ለጽሕፈት ቤቱ በደብዳቤ ተገልጿል።
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ደግሞ ለግንባታ ሥራ የተከፈለ 202 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በድጋሚ ስለመከፈሉ የሚያሳይ መረጃ ተገኝቷል። በመሆኑም ክፍያው ተመላኝ እንዲደረግ እና ይህን የፈፀሙ አመራሮችም በሕግ እንዲጠየቁ የኦዲት መስሪያ ቤቱ ጠይቋል።
በሌሎች 18 ተቋማት ደግሞ በወቅቱ ያልተሰበሰበ አንድ ቢሊዮን ብር ሒሳብ መኖሩ ተደርሶበታል። በተለይ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኤጀንሲ ሊሰበስበው ከሚገባ ሒሳብ ውስጥ 651 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በወቅቱ አለመሰበሰቡ የኦዲት ግኝቱ ያመላክታል። የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣንም ከ282 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር በወቅቱ ያልሰበሰበው ገቢ እንዳለበት በኦዲት ሪፖርቱ ተረጋግጧል።
በሌላ በኩል በ16 የአዲስ አበባ ተቋማት ከ532 ሺህ ብር በላይ ከደንብና መመሪያ ውጭ የተከፈለ የአበልና የደመወዝ ሒሳብ መገኘቱን የአዲት መስሪያ ቤቱ አስታውቋል። በዳግማዊ ምኒልክ ሪፈራል ሆስፒታል ከመመሪያ ውጭ ነው የተባለ የ121 ሺህ ብር የደመወዝ ክፍያ መኖሩን እና በእሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከያና መቆጣጠሪያ
ተቋም በኩል ደግሞ 120 ሺህ ብር ከመመሪያ ውጭ የሆነ የአበል ክፍያ መገኘቱን ሪፖርቱ አሳይቷል።
በተጨማሪም ከሰባት ተቋማት ለማን እንደተከፈለ የማይታወቅ ከ11 ሚሊየን ብር በላይ መገኘቱን ያስታወቀው የኦዲት ሪፖርቱ ፤ በተለይ እሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከያና መቆጣጠሪያ እንዲሁም ቦሌ ክፍለ ከተማ ጽሕፈት ቤት እያንዳንዳቸው ከ5 ሚሊየን ብር ለማን እንደተከፈለ ያልታወቀ ሒሳብ ወጪ ማድረጋቸው ተደርሶበታል።
የኦዲት ሪፖርቱ ከግንባታ ጋር ተያይዞ ቅድሚያ ክፍያ ተከፍሎ ግንባታው ያልተጀመረ ፕሮጀክት መኖሩን ደርሶበታል። በዚህም መሰረት የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀነሲ በራስ መኮንን ድልድይ አካባቢ የተሽከርካሪ ማቆሚያ ለማስገንባት በግንቦት 22 ቀን 2009 ዓ.ም 31 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ቅደሚያ ቢከፍልም ግንባታው ከ2 ዓመታት በላይ ሳይጀመር በመቆየቱ ቅደመ ክፍያው ተመላሽ እንዲደረግ የከተማዋ ኦዲት መስሪያ ቤት በደብዳቤ ማሳሰቢያ አስተላልፏል።
እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት መረጃ መሠረት፤ በኦዲት ግኝቱ ላይ አፋጣኝ ምላሽ ያልሰጡ ተቋማት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ከተገለፀ በኋላ ከ66 ሚሊየን ብር በላይ ተመላሽ የተደረገ ሲሆን፤ ሕጋዊ እርምጃ ባልወሰዱ 27 ተቋማት ላይ ክስ እንዲመሰረት ለፌዴራል ዐቃቤ ሕግ እና ለአዲስ አበባ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ ማስረጃ ተልኳል። መስሪያ ቤቱ በቀጣይ በኮንዶሚኒየም ግንባተዎች ላይ እያከናወነ ያለውን የኦዲት ሪፖርት ሲጠናቀቅ በጥቂት ወራት ውስጥ ይፋ ለማድረግ አቅዷል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 29/2012
ጌትነት ተስፋማርያም