– በሩብ ዓመት ብቻ 168 ሚሊየን ብር ተሰብስቧል
አዲስ አበባ፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማፋጠን ሲባል ተከፍተው የነበሩ 4000 የገንዘብ አካውንቶች በአንድ ቋት መካተታቸው ተገለፀ።
ህዝባዊ ተሳትፎ እንደቀጠለ ሲሆን በ2012 ሩብ ዓመት ብቻ 168 ሚሊየን ብር መሰብሰቡ ተጠቆመ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የህዝብ ግንኙነትና የሚዲያ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም ትናንት በሰጡት መግለጫ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማፋጠን ሲባል በድርጅቶች፣ ተቋማትና ግለሰቦች ተከፍተው የነበሩ ከ4000 በላይ አካውንቶች ለሥራ ያመች ዘንድ በአንድ አካውንት ብቻ እንዲስተናገድ ተደርጓል።
እንደ አቶ ኃይሉ ገለፃ፤ የግድቡ ግንባታ በተፋጠነ ሁኔታ የቀጠለ ሲሆን ህዝባዊ ተሳትፎውም አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል። በ2011 በጀት ዓመት 970 ሚሊየን ብር የተሰበሰበ ሲሆን በ2012 ሩብ ዓመት ደግሞ 168 ሚሊየን 953 ሺህ ብር ገቢ ተገኝቷል። በተለይም በመስከረም 2012 ዓ.ም 82 ሚሊየን ብር ተሰብስቧል። በቀጣይም በአማካይ በየወሩ 100 ሚሊየን ብር የመሰብሰብ ውጥን መኖሩን አመልክተዋል። ቀደም ባሉት ዓመታትም ህዝባዊ ተሳትፎ በነበረበት ወቅትም እስከ 100 ሚሊየን ብር ይሰበሰብ ነበር።
ከገንዘብ ተቋማት ጋር በመሆን ጽሕፈት ቤቱ በስፋት እየሠራና ቃል የተገቡ ሀብቶች ተሸጠው ብሩ እንዲገባ እየተደረገ ነው። ለህዝብ መረጃ በመስጠት ረገድ ክፍተት መኖሩንም በመጠቆም፣ በዚህ ረገድ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በስፋት እንዲሠሩ ጥሪ ቀርቧል። መሥሪያ ቤቶች ተከታትለው ቦንድ ለገዙ ዜጎች ኩፖን አለመስጠታቸው ሌላው ችግር እንደነበር አስታውሰዋል። የቦንድ ግዥ በተመለከተም በርካታ ቅሬታዎች ነበሩ። በአሁኑ ወቅት ግን ሰባት ማይክሮ ፋይናንስ፣ ልማት ባንክ እና ንግድ ባንክ ጋር በመነጋገር አሠራሩ ፈር እንዲይዝ ተደርጓል። እስከ አሁን ቦንድ ለገዙ ዜጎች ስድስት ቢሊዮን ብር ተመላሽ ሆኗል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ በግድቡ ግንባታ ዙሪያ የኢትዮጵያ አካሄድ ሳይንሳዊና የወንዙን የ100 ዓመት ፍሰትን መሰረት በማድረግ የውሃ ሙሌቱን ታሳቢ አድርጋ እየሠራች ነው። ግብፅ ከዲፕሎማሲ ስትወጣ መስመር እንድትይዝ እየተደረገ መሆኑንም አብራርተዋል። ‹‹እየገነባን ያለነው ግድብ እንጂ ስታዲየም አይደለም›› ለዚህም ግድቡ ውሃ እንዲይዝ በሳይንሳዊ መንገድ እንሠራለን ብለዋል።
ግብፅ በአባይ ላይ እምነት በማጣቷም ሦስተኛ አደራዳሪ መፈለጓንም ጠቁመዋል። ይሁንና የሚደራደሩት ባለሙያዎች በመሆናቸው ኢትዮጵያ አሁንም በፍትህ አደባባይ አሸናፊ ትሆናለች፤ ብሔራዊ ጥቅሟንም አሳልፋ አትሰጥም ነው ያሉት።
ግብፅ ጉዳዩን በፖለቲካ ዓይን ከማየት በዘለለ ሌላ እይታ እንዲኖረው አትፈልግም። ይሁንና ግድቡ እውን እንዲሆንም የኢትዮጵያም ህዝብና መንግሥት ወሳኝ ሚና እንዳላቸው አብራርተዋል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ የግድቡ መሰረተ ድንጋይ ሲቀመጥ በ80 ቢሊዮን ብር
ለማጠናቀቅ ታስቦ የነበረ ሲሆን፤ እስካሁን 99 ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል። ግድቡን ለማጠናቀቅ ደግሞ 40 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ ይጠይቃል። ለግድቡ ግንባታ 15 ከመቶ የሚሆነውን ገንዘብ ከህዝቡ ለመሰብሰብ የታቀደ ሲሆን እስካሁን 13 ቢሊዮን ብር ከህዝቡ መሰብሰቡ ይታወቃል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 29/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር