አዲስ አበባ፡- ለረጅም ጊዜ ገንዘብ ሚኒስቴር፣ ዩኒቨርሲቲውንና ባለድርሻ አካላትን ሲያከራክር የነበረው የሠመራ ዩኒቨርሲቲ የ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ማስፋፊያ ፕሮጀክት ወደ ተግባር መግባቱ ተገለፀ።
ግንባታው ቢጀመርም የኮንትራክተሮች አቅም ውስንነትና የውጭ ምንዛሪ እጥረት አሁንም እንቅፋት መፍጠሩ ታውቋል።
በሠመራ ዩኒቨርሲቲ የግንባታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዳይሬክተር ኢንጅነር ረሺድ አህመድ በተለይም ለጋዜጣው ሪፖርተር እንደገለፁት፤ ሠመራ ዩኒቨርሲቲ ከዓመታት በፊት ዲዛይን አድርጎ የ2 ነጥብ 5 በሊዮን ብር ማስፋፊያ ፕሮጀክት ቢያቀርብም ከተጠየቀው ገንዘብ አኳያ ከፍተኛ ክርክር የነበረበት መሆኑን አስታውሰዋል።
ሆኖም ግንባታው አስፈላጊነቱ በመታመኑ በአሁኑ ወቅት ሥራው እየተከናወነ ነው። ለግንባታው የተጠየቀው በጀት የተጋነነ ነው በማለት ተቃውሞ አስነስቶ እንደነበርና ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋርም ከፍተኛ ክርክር እንደተደረገበት አስታውሰዋል።
ይሁንና የሥራው አስፈላጊነት ታምኖበት በ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ማስፋፊያ ፕሮጀክቱ እንዲከናወን ተወስኗል። ግንባታው የተማሪዎች ማደሪያ፣ የተማሪዎች መመገቢያ፣ ቤተ መጽሐፍትና የመምህራን መኖሪያና ሌሎችንም ያካተተ እንዲሆን ተደርጓል።
እንደ ኢንጅነሩ ገለፃ፤ ግንባታው ዘመናዊ አሠራሮችን የሚከተል ሲሆን እስከ 40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ የሚደርሰውን የአካባቢውን ሙቀት እንዲቋቋም ታሳቢ በማድረግ ዲዛይን ተደርጓል። በዚህም መሰረት ከበጀቱ ውስጥ ከ35 እስከ 40 ከመቶ የሚሆነው ለኤሌክትሮ መካኒካል ሥራዎችን ሥራ ወጭ የሚደረግ ነው። በተለይም ለማዝቀዣና መሰል ሥራዎች ከፍተኛ በጀት ይጠይቃል።
ኢንጂነሩ እንዳሉት፤ ዩኒቨርሲቲው በ2012 ዓ.ም በሁሉም መርሐ ግብሮች 18ሺ ተማሪዎችን ተቀብሎ እንዲያስተምር አቅጣጫ የተቀመጠ ቢሆንም ሰፊ የሆነ የማስፋፊያና አዳዲስ ግንባታዎች ብሎም አስፈላጊ ግብዓቶች እጥረት ማነቆ ሆነውበታል።
ከዚህ በተጨማሪም በክልሉ ብቸኛው ዩኒቨርሲቲ በመሆኑ አርብቶ አደሩንና ከፊል አርብቶ አደሩን ሕይወት የሚቀይሩ ምሁራንን እንዲያፈራና ምርምሮችንም እንዲያካሄድ ትልቅ ኃላፊነት ተጥሎበታል። ለጅቡቲ እና ኤርትራ በቅርበት የሚገኝ በመሆኑም ዓለም አቀፍ እይታ እና ተግባር ያለው ዩኒቨርሲቲ መሆን ይጠበቅበታል።
ከዚህ አኳያ በቂ የተማረ ሰው ኃይል በብዛት ለማቅረብና ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እንደሚገባ በማመን ትልቅ ኢንቨስትመንት እየተካሄደ መሆኑን አውስተዋል።
እንደ ኢንጅሩ ገለፃ፤ ሥራዎቹ በተሻለ ፍጥነት እንዲከናወኑ ፍላጎት ቢኖርም ችግሮች እያጋጠሙት መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይም የሥራ ተቋራጮች አቅም ውስንነት አንዱ ችግር ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በርካታ ግብዓቶች ከውጭ አገር የሚገቡ በመሆናቸው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሥራውን እየተፈታተነ መሆኑን አብራርተዋል። በተለይም የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት የሚደረገው ጥረት አድካሚ በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡት አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 29/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር