አዲስ አበባ፦ የመውሊድ በአል ሲከበር ህዝበ ሙስሊሙ ሀገሪቱ ካጋጠማት ወቅታዊ ችግር በሰላም፣ በፍቅርና በአንድነት እንድትወጣ በመጸለይና የተቸገሩትን በመርዳት መሆን እንዳለበት ተገለጸ።
ቅዳሜ ጥቅምት 29 ቀን 2012 ዓ.ም የሚከበረውን 1494ኛውን የመውሊድ በአል አስመልክቶ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ባስተላለፈው የ“እንኳን አደረሳችሁ!” መልእክት የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ኡመር እድሪስ እንደተናገሩት፤ በአሉ ህዝበ ሙስሊሙ ስለእምነቱ ምክር የሚወስድበት፣ ሙስሊም ከሙስሊም ብቻ ሳይሆን ሙስሊም ከክርስቲያን የሚተሳሰርበት፣ ብሎም ለሀገር ሰላምና እድገት ጸሎት የሚደረግበት ነው። በመሆኑም፣ ህዝበ ሙስሊሙ በአሉን ሲያከብር እርስ በእርስ በመተሳሰብ፣የተቸገሩ ወገኖቹን በመርዳትና ስለሀገርና ስለህዘብ ሰላምና አንድነት በመጸለይ ሊሆን ይገባል።
“በአሁኑ ወቅት ያለው የሀገሪቱ ሰላምና የአንድነት ጉዳይ አሳሳቢ ነው” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ አንድነት ከሌለ ሰላም፣ ሰላምም ከሌለ ልማት አይኖርም። በመሆኑም፤ አንድነትንና ሰላምን ማስጠበቅ ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ይሆናል። ወጣቱ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የመንግስት አመራሮችና መላው ህዝብ በሀገሪቱ መከባበርና መተዛዘን እንዲኖር መጸለይና መስራትም ይጠበቅበታል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ መውሊድ በውዴታ የሚከበር በአል በመሆኑ የማያከብሩ ወገኖች እንዳሉ ይታወቃል። በመሆኑም፤ አክባሪውንም ከመከልከልም ሆነ እርስ በእርስ ከመዘላለፍ መቆጠብ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በተጨማሪም፤ ምክር ቤቱ ከፌዴራል መጅሊስ ጀምሮ የክልልና የከተማ መስተዳድር መጅሊስ ምክር ቤቶችን የማዋቀር ሂደት ጀምሯል። ሂደቱም የሁሉንም ክልሎችና የከተማ መስተዳድር መጅሊስ ምክር ቤቶችን የሚመለከት በመሆኑ ስርአትን በጠበቀና ሰላምን በማያናጋ አኳኋን በእርጋታና በጥበብ እየተሰራ ነው። እስካሁንም በኦሮሚያ፤ በደቡብና በአዲስ አበባ ሶስት መጅሊሶች የተዋቀሩ ሲሆን፤ በተቀሩት ክልሎችም በተያዘላቸው እቅድ መሰረት የሚዋቀሩ ይሆናል።
ስለዚህ፤ ማእከልን ባልጠበቀ አኳኋን የመጅሊስ ምክር ቤቶችንና መስጅዶችን መንጠቅ፤ በከተሞች ኢማሞችንና ሙአዚኖችን፤ በገጠር መሻኢኮችንና ሙደሪሶችን በማስከፋት ከስራ የማፈናቀል ድርጊት ተቀባይነት የሌለው ነው በማለት ከዚህ ተግባር መቆጠብ እንደሚገባ አሳስበዋል። መንግስትም ተገቢውን የመቆጣጠር ስራ መስራት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 28/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ