የዋጋ ንረቱ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች የሚጎዳ መሆኑን በማስታወስ መንግሥት ይህንን ለመቆጣጠር በከፍተኛ ትኩረት የሚሠራ መሆኑን ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በፓርላማው መክፈቻ ንግግራቸው ከገለጹ አንድ ወር ሆኗል፡፡
ችግሩን ለማቃለል መሰረታዊ የምግብ ሸቀጦችን በበቂ መጠን ከውጭ ለማስገባት መታቀዱንም ጠቁመው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ፤ “በተያዘው ወር የሸቀጦች ዋጋ 18 ነጥብ አምስት በመቶ ማደጉን የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ገልጿል” ብለው የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል፡፡ ይህንን መሰረት አድርገን የተለያዩ የኢኮኖሚ ባለሙያዎችን አነጋግረናል፡፡
የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ሸዋፈራው ሽታሁን እንደሚናገሩት፤ የወቅቱ የዋጋ ንረት መንስኤው ኢኮኖሚያዊ ያልሆነ እና ኢኮኖሚያዊ የሆነ ነው:: ኢኮኖሚያዊ ያልሆነው ፖለቲካዊ መነሻ ሲሆን፤ ሰዎች ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት እንዳላቸው ቢቀመጥም የመንቀሳቀስ መብታቸው ተገድቦ መቆየቱ ኢኮኖሚውን አዛብቶታል፡፡ ይህም የኑሮ ውድነትን አስከትሏል፡፡
ለምሳሌ፤ በምሥራቅ ሐረርጌ በሃያ ወረዳዎች ላይ በነበረ ግጭት በባቢሌ ወረዳ የሰባት ቀበሌ ገበሬ ማህበር ገበሬዎች ወደ ከተማ በመሄዳቸው የዘሩትን ማጨድ አለመቻላቸው በምርት ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ ቡናም በነበረው ግጭት ምክንያት ተገቢው እንክብካቤ አልተደረገለትም፡፡ ስለዚህ ያ የተከማቸ ያልተሠራ ውዝፍ ሥራ የምርት አቅርቦት በማሳጠሩ የዋጋ ንረት አስከትሏል፡፡
ሰውና ምርት እንደፈለጉ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ አልቻሉም ነበር፡፡ ጤፍ ከሚገኝበት አካባቢ እንደልብ ወደማይገኝበት አካባቢ መንቀሳቀስ አለበት፡፡ ያ አለመሆኑ እጥረት ፈጥሯል፡፡ አንዳንዴ ሆነ ተብሎ ሰው ሠራሽ በሆነ መልኩ ከአንዳንድ ክልሎች ምርት የማይወጣበት ሁኔታ አለ፡፡ በዚህም ሰበብ ምርቱን የያዘው አካልም ሆነ ምርቱን መግዛት እየፈለገ ማግኘት ያልቻለው አካል ተጎጂ ከመሆናቸው አልፎ በገበያው ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
“የአገሪቷን ኢኮኖሚ የብሔር ፖለቲካ ድባቅ እየመታው ነው” የሚሉት አቶ ሽዋፈራው፤ የ21ኛው ክፍለ ዘመን እሳቤ በመተባበር ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ገበያው ጤናማ መስተጋብራዊ ግንኙነት ይፈልጋል፡፡ ይህ እንዳይሆን ፖለቲካው ገድቦታል:: ህገመንግሥቱ፣ ፖለቲከኞች፣ መገናኛ ብዙሃን ሁሉም ቢናገሩም በተግባር ግን መልካም አስተዳደር የለም፡፡ አገልግሎቶች በአብዛኛው የሚቀርቡት በመንግሥት ነው፡፡
መብራት፣ ውሃ እና ሌላውም አገልግሎት የሚሰጠው በመንግሥት ነው፡፡ ሀብቱ እንኳን ቢኖር የመንግሥት ቢሮክራሲ አገልግሎቶች በአግባቡ እንዳይሰጡ ማድረጉ በኑሮ ውድነቱ ላይ ሚና ይኖረዋል ይላሉ፡፡
“ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ ባለችው ደብረብርሃን የተመረተው ምርት በቀጥታ ለአዲስ አበባ ሸማች የሚቀርብበት ሁኔታ ቢፈጠር ጥሩ ነው::” በማለት በምሳሌ የሚያስረዱት አቶ ሽዋፈራው፤ ደላላን ከመሃል ቆርጦ ማውጣት ቢቻል የኑሮ ውድነቱ ይቀንሳል፡፡ በእርግጥ ነጋዴ ሰው ነው መጠቀም ያለበት፡፡
ነገር ግን ሥራው የህግ ተቃርኖ ሊኖረው አይገባም፡፡ በእያንዳንዱ ገበያ ላይ የሠላሳ በመቶ ጭማሪ የሚመጣው በደላላ ምክንያት በመሆኑ ከገበሬ ወደጅምላ ሻጭ፣ ከጅምላ ሻጭ ለቸርቻሪ፤ ከቸርቻሪ ደግሞ ለሸማቹ የሚሄድበት ረዥም ሰንሰለት ከነትራንስፖርቱ ሲሰላ ከአምራቹ ወደሸማቹ እስከሚደርስ በተለይ በመሰረታዊ ሸቀጦች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የሚያስከትል በመሆኑ ሰንሰለቱ የሚያጥርበት ሁኔታ መኖር እንዳለበትም ነው የጠቆሙት፤ ለምሳሌ፤ እንደምርት ገበያ ዓይነት አምራችና ሸማች የሚገናኙበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል ካሉ በኋላ፤ መንግሥት አገርን የሚመራበት መንገድ በፈጠራ የታጀበ መሆን እንደሚገባውም ተናግረዋል::
ከኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ውስጥ የውጭ ምንዛሬ አንደኛው መሆኑን በማስታወስ፤ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ግድ እንደሚል ያመለክታሉ፡፡ “እጥረቱ ያጋጠመው አገሪቷ ስለግብርና ማውራት እያለባት ከአቅሟ በላይ የኢንዱስትሪ ፓርክ እየገነባች ስለፋብሪካ በማውራቷ ነው” የሚሉት አቶ ሽዋፈራው፤ “በኢትዮጵያ ሁኔታ መሬትን ትቶ ኢኮኖሚን የትም ማድረስ የማይቻል በመሆኑ ከአቅም በላይ ከመንጠራራት ይልቅ መሬትን በአግባቡ ማልማት የሚቻልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይገባል” ይላሉ፡፡
“የኢትዮጵያ ገበሬ ያለው መሬት ታቅፎ ነው:: አጠቃላይ ህዝቡን የመመገብ አቅም የለውም፡፡” የሚሉት አቶ ሽዋፈራው፤ “ስለዚህ ገበሬው መሬት እንደያዘ ከባለሀብቱ ጋር ተቀናጅቶ በገጠር አክሲዮን ማህበራት የሚያቋቁሙበት ዕድል ቢመቻች የተሻለ ውጤት ማምጣት ይቻላል፡፡ ገበሬው እና የገበሬው ልጅ እዚያው ሥራ ያገኛሉ፡፡ ወደ አዲስ አበባ የሚፈልሰው ቁጥርም ይቀንሳል፡፡
ስለዚህ ትልቁ መፍትሔ ያለው መሬትንና የሰው ኃይል ሀብትን ፈጠራ በተሞላበት መልኩ አቀናጅቶ መጠቀም ላይ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ ከመንግሥት በተጨማሪ ህዝቡም የሥራ እና የቁጠባ ባህሉን ሊያሻሽል እንደሚገባም ያሳስባሉ፡፡
በፖሊሲ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ተመራማሪው ዶክተር ፀጋዬ ገብረ ኪዳን፤ በዋናነት የኑሮ ውድነት መንስኤው የፍላጎት እና የአቅርቦት አለመጣጣም መሆኑን በመጠቆም፤ በኢትዮጵያም የአምራቹ ወጪ መጨመር፤ አቅርቦት ሳይጨመር የፍላጎት ማደግ የኑሮ ውድነቱን እንዳስከተለ ያብራራሉ፡፡
እንደዶክተር ፀጋዬ ገለጻ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የዋጋ ውድነት የተፈጠረው የአምራቹ ዘርፍ በቂ ምርት ባለማቅረቡ፤ መንግሥት ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ሲቀርፅ፤ ሠራተኛ ሲቀጥር ገንዘብ ስለሚረጭ ፍላጎት ማደጉ እና አምራቾች የውጭ ምንዛሬ እጥረት በመኖሩ በፈለጉት ጊዜ ጥሬ ዕቃ አለማግኘታቸው፤ እንዲሁም የኃይል አቅርቦት ችግር ምርቱ እንዲቀንስ አድርጓል፡፡
እንደ አቶ ሸዋፈራው ሁሉ፤ “በየአካባቢው ያለው አለመረጋጋትም ምርቶች ከቦታ ቦታ እንደልብ አለመንቀሳቀሳቸው ለዋጋ ንረቱ አስተዋፅኦ አድርጓል” የሚሉት ዶክተር ፀጋዬ፤ በአጠቃላይ ባለፉት አስር ዓመታት የነበረው ባለሁለት አሃዝ የዋጋ ግሽበት መነሻው የፍላጎት ዕድገት ነው፡፡ በተለይ፤ የመንግሥት የመሰረተ ልማት ግንባታ የፈጠረው የዋጋ ግሽበት ሲሆን፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የምርት መቀዛቀዝ እና ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ አለመቻል ነው” የሚል እምነት እንዳላቸው ይገልጻሉ፡፡
ሌላው፤ “የህዝቡ የቤት ፍላጎት እና ያለው የቤት አቅርቦት የተመጣጠነ አለመሆን አምራቾችና ነጋዴዎች ከፍተኛ የቤት ኪራይ ዋጋ ሲከፍሉ ዋጋውን በሸማቹ ላይ ስለሚጭኑ የኑሮ ውድነቱ ተከስቷል” ብለዋል፡፡
ዶክተር ፀጋዬ፤ መፍትሔው የግሉ ዘርፍ ምርታማነት መጨመር ሲሆን፤ ከኃይል መቆራረጥ ጀምሮ ያሉትን ችግሮች ማስተካከልም ተገቢ ነው:: የአጭር ጊዜ መፍትሔው ደግሞ፤ በመንግሥት እንደተገለጸው ከውጭ መሰረታዊ ሸቀጦችን ለማስገባት ተሞክሮ ያልተሳካ በመሆኑ ለአምራቾች ብቻ ሳይሆን ለአስመጪዎች የውጭ ምንዛሬ በመስጠት ነጋዴው ራሱ እንዲያስገባ ማድረግ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
ብሔራዊ ባንክ ዕድገትን ብቻ ሳይሆን የዋጋ ግሽበትንም መቆጣጠር አለበት የሚሉት ዶክተር ፀጋዬ፤ዕድገት ቢያስፈልግም በተመጣጠነ መልኩ የዋጋ ግሽበትንም መቆጣጠርና ማመዛዘን እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡ ዕድገት መቀነስ ባይኖርበትም ትልልቅ መሰረተ ልማቶች በከፍተኛ ጥንቃቄ መካሄድ አለባቸው፡፡ በብድር ቢገነቡም ገንዘብ ስለሚሰራጭ እና በፍላጎቱ መጨመር ላይ ሚና ስለሚኖራቸው በጥንቃቄ መታየት አለባቸው ብለዋል፡፡
የመንግሥት የቤቶች ግንባታ በ14 ዓመት ብክነት እንጂ ሰፊ ለውጥ ማምጣት ባለመቻሉ የኪራይ ዋጋ አልተስተካከለም የሚሉት ዶክተር ፀጋዬ፤ መሬቱን ምክንያታዊ በሆነ ዋጋ ለግሉ ዘርፍ በማቅረብ እና በመሃል አዲስ አበባ መሬቱን የያዙ ሰዎች ድርሻ እንዲኖራቸው በማድረግ በስፋት በባለሀብቶች በመገንባት ገበያውን ማረጋጋት ይቻላል በማለት ሃሰባቸውን ያጠቃልላሉ፡፡
በመሆኑም፤ አሁን ያለውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት በመንግሥት ከተያዘው መሰረታዊ ሸቀጦችን ከውጭ የማስገባት አማራጭ ባሻገር፤ ባለሙያዎቹ እንዳሉት፤ ሰዎችና ምርት እንደፈለጉ የሚንቀሳቀሱበትን ሁኔታ ማመቻቸት፤ መሬትንና የሰው ኃይልን ፈጠራ በታከለበት መንገድ መጠቀም ተገቢ ነው። በተጨማሪም፤ ፖለቲካውን እና ቢሮክራሲውን በማስተካከል የህዝቡን ችግር ማቃለል፤ እንዲሁም፤ የህብረተሰቡን የሥራና የቁጠባ ባህል በማሳደግ ግሽበቱን መቆጣጠር ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 28/2012
ምህረት ሞገስ