አዲስ አበባ፡- የመደመርን እሳቤ መነሻ ያደረገው አዲሱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በቀጣናው በየጊዜው ተለዋዋጭ ለሆነው የጂኦ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ምቹ መሆኑ ተገለጸ፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ተንታኝ አቶ መሐመድራፊ አባራያ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በቅርቡ የተዘጋጀው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የመደመርን እሳቤ ያካተተ ሲሆን፤ በመከላከያ ላይ ትኩረት የሚሰጥ፤ በአንጻሩ ደግሞ የዲፕሎማሲና የሁለትዮሽ ሥራዎችን ለማጠናከርም የታሰበ በመሆኑ ኢትዮጵያ ለምትገኝበት የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የጂኦ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ምቹ ነው፡፡
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ የመደመር የውጭ ግንኙነት እሳቤ በዋነኛነት የ1994 ዓ.ምን የውጭ ግንኙነትና ደኅንነት ፖሊሲ በጎ ጎኖች አስጠብቆ ማስቀጠል፤ እንዲሁም የነበሩትን ክፍተቶች የማስተካከል ዓላማ ያነገበ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የነበረው የውጭ ግንኙነትና የአገራዊ ደኅንነት ፖሊሲ በወቅቱ አገሪቱ የነበረችበትን ተጨባጭ ሁኔታና ቀጣናዊ እውነታዎች መሰረት ያደረገ በመሆኑ፤ የአሁኑን ነባራዊ ሁኔታ አካታች በማድረግ በመደመር እሳቤ እንዲቃኝ ተደርጓል፡፡
የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጠንካራ የሆነ የደኅንነትና የመከላከያ አቅጣጫዎችን ተከትሎ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን ያብራሩት አቶ መሐመድራፊ፤ በነበረው ፖሊሲም ይህ ነው የሚባል ጎልቶ የመጣ የብሄራዊ ደኅንነት ስጋት አለመኖሩን እንደ ጥንካሬ አንስተዋል፡፡
በአንጻሩ፤ በተለያዩ ዓለማት ያሉትን ዜጎች ክብር ከማስጠበቅና ከአገራት ጋር የኢኮኖሚ ግንኙነቶችን ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ፤ እንዲሁም ኢትዮጵያ እንደአገር በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትፈልገውን ተሰሚነት ከማጉላት አንጻር እምብዛም እንዳልሆነ አመላክተዋል፡፡
አቶ መሐመድራፊ እንደሚሉት፤ የቀድሞው ፖሊሲ ሲቀረጽ በወቅቱ አገሪቱ ከኢትዮ – ኤርትራ ጦርነት ያገገመችበት ጊዜ ነበር፡፡ አንዳንድ የአፍሪካ አገራት ያልተረጋጉበት፤ እንዲሁም በቀጣናው አንዳንዶች መንግሥት የሌላቸው ስለነበሩ በአብዛኛው የመከላከልና ብሔራዊ ደኅንነትን ትኩረት ሰጥቶ የወጣ ፖሊሲ ነበር፡፡
ከዚህ በተጨማሪ፤ ድህነት ቅነሳና የስጋት ተጋላጭነትን መከተል የፖሊሲው አምዶች ነበሩ፡፡ በመሆኑም፤ እሳቤው ከጎረቤት አገራት ጋር ተባብሮ በጋራ በመሥራት ረገድ ብዙም ትኩረት ያላደረገ ነበር፡፡ የምሥራቅ አፍሪካንና ቀይ ባህርን አካባቢ የጠላት ቀጣና አድርጎ የመመልከት አዝማሚያም ነበረው፡፡ ከአገራት ጋር የነበረውን ግንኙነትም በጥርጣሬ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
መደመርን መነሻ ያደረገው የአሁኑ የውጭ ጉዳይ እሳቤ በተለያዩ አገራት የሚገኙ ዜጎችን ጥቅም ለማስከበር፣ የዲፕሎማቶችን አቅም ማጎልበት፣ በቀጣናው ላይ የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠርና ሰላማዊ ግንኙነቶችን ለማደስም ትልቅ ሚና እንዳለው አቶ መሐመድራፊ ገልጸዋል:: “ቀጣናውን መልካም የትበብር መድረክ አድርጎ በማሰብ፤ እንዲሁም ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን ተሰሚነት ለማጎልበትና ለማጠናከር ይረዳል” ብለዋል፡፡
ከአገራቱ ጋር ባለው ግንኙነት መልካም ድሎች ለማምጣትና እሳቤውን ለማሳካትም ጠንካራ የኢኮኖሚና የዳበረ የመከላከያ አቅም መገንባት ታሳቢ መደረጉን አቶ መሐመድራፊ ገልጸዋል፡፡ አክለውም የመደመር የውጭ ግንኙነት እሳቤ “የገር ኃይል” የሚባሉት አማራጮች በሆኑ ስፖርታዊ ክንውኖች፣ የጥበብ ሥራዎች የባህል ትውውቆችና የሚዲያ አካላት ኢትዮጵያ እንደ አገር ሊኖራት የሚገባውን ተሰሚነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊያቀዳጇት እንደሚችሉ ጠቅሰዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 28/2012
አዲሱ ገረመው