የኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ሜዳና ተራራ በሚዘናፈለው የጤፍ፣ የስንዴ፣ የገብስ እና ሌሎች የመኸር ሰብሎች ተሸፍኖ ሲታይ መንፈስን ያረካል፤ ዓይንን ያጠግባል፡፡ በኤጀሬ ወረዳ ዳሞቱ ቀበሌ በኩታ ገጠም እርሻ የተቀናጁ አርሶአደሮች በአሲድ የተጠቃ መሬታቸውን በኖራ በማከም የዘሩት ገብስና ባቄላ ምርታማነቱ የመንደሩን ሰዎች ሁሉ አጀብ አስብሏል፡፡
ወይዘሮ አለሚቱ ሶሪታ በ20 ሄክታር መሬት ላይ በኩታ ገጠም ከተደራጁት 86 አርሶ አደሮች ውስጥ 14 እማወራዎች አንዷ ናቸው፡፡ በግብርና ባለሙያዎች በተሰጣቸው ምክርና ድጋፍ በኩታገጠም እርሻ ተቀናጅተው በኖራ በታከመው መሬታቸው የዘሩት ገብስ በአካባቢው የተለየ ውጤት እንዲያዩ አድርጓቸዋል፡፡
«ባለሙያዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ከማሳዬ ላይ የአፈር ናሙና ሲወስዱ ለምንድ ነው? የምትወስዱት ስላቸው ‹መሬቱን ለማከም ነው› ሲሉኝ አልተዋጠልኝም ነበር፡፡ አሁን ግን ይህንን ተአምር ካየሁ በኋላ ለካስ መሬትም ይታከማል፤ ምርትም ያምራል እንድል አድርጎኛል፤ አስገርሞኛልም» ይላሉ ወይዘሮዋ፡፡
ቀደም ሲል በሄክታር ከ5 እስከ 7 ኩንታል እንደሚያገኙ የተናገሩት አርሶአደሯ አሁን ግን ከ30 እስከ 40 ኩንታል የማግኘት ተስፋ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ ለዚህም ውጤት የሆለታ የግብርና ምርምር ማዕከልን አመስግነዋል፡፡
አርሶአደር ተስፋዬ መላኩ እንደ ወይዘሮ አለሚቱ ሁሉ ከማዕከሉ የመጡ ባለሙያዎች ምርታማ ያልሆነ መሬትን በኖራ በማከም ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚቻል ሲያስተምሩት ጆሮውን አለመስጠቱን ይናገራል፡፡ «አሁን ተስፋዬ ቴክኖሎጂው ምርታማነትን እንዲህ የሚጨምር ከሆነ አርሶ አደሩ ኢኮኖሚያዊ ሕይወቱ ይለወጣል» ሲል ተስፋውን አመልክቷል፡፡
የኤጄሬ ወረዳ የአፈር ልማት የሥራ ሂደት መሪ አቶ ባይሳ አዱኛ እንደሚሉት በወረዳው አንዳንድ የእርሻ መሬቶች በአሲድ በመጠቃታቸው ምርታማ አይደሉም፡፡ ከሆለታ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር አርሶ አደሩን በኩታ ገጠም በማደራጀት አፈርን በኖራ የማከምና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀም ማድረግ ተችሏል ይላሉ፡፡ ከዚህ ሁሉ ሂደት በኋላ አርሶ አደሩ ባገኘው ውጤት እርካታ ማግኘቱንም ይገልጻሉ፡፡
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ደረጃው ቢለያይም ሀገሪቱ ካላት አጠቃላይ የእርሻ መሬት 43 በመቶ የሚጠጋው በአሲድ ይጠቃል፡፡ ይህ ተጋላጭነት በተለይም በሀገሪቱ በደቡብ ምዕራብ፣ በደቡብ ክልል፣ በአማራ ክልል በምሥራቅ ጎጃምና ደቡብ ጎንደር፣ በመካከለኛው የሀገሪቱ ክፍል በምዕራብ ሸዋ ዞን ጎልቶ እንደሚታይ ይታመናል፡፡
በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የግብርና ኤክስቴንሽንና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደረሰ ተሾመ ተቋሙ በአሲድ የተጠቁ መሬቶችን በኖራ የማከም ቴክኖሎጂን የማስተዋወቅ ሥራን በመስራት አመርቂ ውጤት ማግኘቱን ይናገራሉ፡፡ ግብርናው የምግብ ዋስትናችንን ለማረጋገጥ በተለይ በአሲድ የተጠቁ መሬቶችን በኖራ በማከም ምርታማነትን ማሳደግ አንድ አማራጭ መሆኑን ጠቅሰዋል::
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ድሪባ ገለቴ አርሶ አደሩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በፍጥነት ተቀብሎ ወደ ሥራ የመግባት ችግር እንዳለበት ጠቅሰው፣ መንግሥት በግብርናው ዘርፍ የያዘውን አቅጣጫ እውን ለማድረግ የገበሬው ንቁ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል በቅርበት መገኘቱ ለአርሶ አደሩ እንደ ጥሩ አጋጣሚ ስለሆነ የዕድሉ ተጠቃሚ በመሆን ምርቱን ለማሳደግ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡ አርሶ አደሩ በቴክኖሎጂዎች የመጠቀም ፍላጎቱ እየጨመረ በመጣ ቁጥር የምርምር ውጤቶችም በዚያው ልክ እንደሚያድጉና ማዕከሎች ሁልጊዜም ከአርሶ አደሩ ጎን በመቆም ድጋፍ እንደሚሰጡ ዶክተር ድሪባ ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 27/2012
ኢያሱ መሰለ