የሕይወት ኡደቱን በአፋርና ሶማሌ ክልል እየጨረሰ ሰሞኑን ወደ ትግራይ፣ አማራና ኦሮሚያ ክልሎች የሚተመው የአንበጣ መንጋ በሰብል ምርቶች ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡ መንጋው በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ማህበረሰቦች ሥራቸውን ገትተው ሰብሎችን ከጥቃት
ለመከላከል ግብግብ ገጥመዋል፡፡ በተቀናጀ መልክ ወረርሽኙን ከጥፋት የመከላከል ሥራ እየተሰራ ሰብሉን ከጥቃቱ ማትረፍ እንደተቻለና አሁንም በአንዳንድ አካባቢዎች ትንቅንቁ እንደቀጠለ ይገለፃል፡፡
የአንበጣ መንጋ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በትግራይ ክልል እንደተከሰተ ይገልፃሉ፤ የደቡብ ትግራይ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ረዳኢ ሀለፎም፡፡ መንጋው በሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በተቀናጀ መልክ በመከላከል ሥራ ላይ እንደተሰማራም ይናገራሉ፡፡ አንበጣው ተደላድሎ እንዳይቀመጥና እንዳያርፍ በባህላዊ ዘዴዎች እረፍት በመንሳት፣ ኬሚካል በመርጨትና ባረፈበት ቦታ በመጨፍጨፍ ከአካባቢው የማስወገድ ሥራ እንደተሰራ ጠቅሰዋል፡፡
የአንበጣው መንጋ ባለበት ወረዳና ዞኖች የሚገኙ ብቻ ሳይሆኑ የትግራይ ሕዝብ ከያለበት ቦታ ወደ ተከሰተበት ሥፍራ በመሄድ ሰብሉን ከመንጋው ጥፋት እየታደገ ነው ብለዋል፡፡ መንጋው አሁንም እንቅስቃሴው ባይቋረጥም ኅብረተሰቡ በንቃት እየተከታተለው የማባረር ሥራውን እየሰራ እንዳለ የተናገሩት አቶ ረዳኢ ከመጨፍጨፍ የተረፈው አንበጣ ወደ ሌላ የትግራይ ዞን እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ዶክተር ሰለሞን አሰፋ የአማራ ክልል ምክትል ግብርና ቢሮ ኃላፊ በበኩላቸው የአንበጣ መንጋው ወደ ክልሉ መግባት የጀመረው ካለፈው ሰኔ ወር ጀምሮ መሆኑን ጠቅሰው፣ የክልሉ ግብርና ቢሮ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመተባበር በአፋር አጎራባች ወረዳዎችና ቀበሌዎች የአሰሳ ሥራ በመሥራት በባህላዊ መንገድ በማባረር እንዲሁም በሰው ኃይልና በአውሮፕላን ኬሚካል የመርጨት ሥራ ሲካሄድ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
የአካባቢው መልክዓ ምድር አምቺነት ስለሌለው አመርቂ ሥራ ለመስራት አለመቻሉን የጠቆሙት አቶ ሰለሞን በክልሉ የተጠቁት አካባቢዎች ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎና ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ሲሆኑ በአጠቃላይ በ9 ወረዳዎች መንጋው እንደተከሰተ ገልጸዋል፡፡
ወደ ክልሉ የገባው የአንበጣ መንጋ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ርብርብ እየተደረገ ቢሆንም ምንጩ ላይ በሚፈለገው ደረጃ ስላልተሰራ መንጋውን ሙሉ ለሙሉ ማቆም አልተቻለም ይላሉ፡፡ በአፋርና ሶማሌ ክልል ያለውን የአንበጣ መንጋ ማጥፋት ከተቻለ መንጋውን ለማጥፋት እንደማይከብድ አስረድተዋል፡፡
አቶ ደጀኔ ሂርጳ በኦሮሚያ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የእጽዋት ጥበቃ ዳይሬክተር በበኩላቸው የአንበጣ መንጋ በሀገራችን ካለፈው ዓመት መጨረሻ ወራት አካባቢ ጀምሮ መከሰት እንደጀመረ ገልጸው በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ዞኖችም እስከ አሁን በ12 ወረዳዎች በሚገኙ 128 ቀበሌዎች ላይ መጠነኛ የጥቃት ሙከራ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ ይሁንና ኅብረተሰቡ ባደረገው ርብርብ በባህላዊ መንገድ ለአንበጣው መንጋ ምቾት በመንሳት፣ በሰው ኃይልና በአውሮፕላን ኬሚካል በመርጭት የከፋ ጉዳት እንዳይከሰት የመከላከል ሥራ መሠራቱን አስታውሰዋል፡፡
በግብርና ሚኒስትር የዕጽዋት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ዘብዲዮስ ሰለቶ እንዳስረዱት፣ የአንበጣው መንጋ በአፋርና በሶማሌ ክልል መኖሩ ከታወቀ ከሰኔ ወር ጀምሮ ባለሙያዎችን ወደ ቦታው በማሰማራት በአውሮፕላን የተደገፈ ኬሚካል የመርጨት ሥራ ሲሰራ እንደነበር እና አሁንም እንደቀጠለ ተናግረዋል፡፡
መንጋው ዕድገቱን ጨርሶ ወደ ምሥራቅ አማራና ደቡባዊ ትግራይ አካባቢዎች በመሰማራቱም በእነዚህ አካባቢዎች የሚያደርሰውን ጥቃት የመከላከል ሥራ እየተሰራ እንዳለ ገልጸዋል፡፡ ለአውሮፕላን አመቺ ባልሆኑ ተራራማ አካባቢዎች በሰው ኃይል በመታገዝ ለመከላከል እየተሞከረ ነው ብለዋል፡፡
ባስተላለፉት መልዕክትም የአንበጣን መንጋ ካለበት ቦታ ማበረር ብቻ ሳይሆን በሚያድርበት ቦታ ተገኝቶ በተለያዩ ዘዴዎች ቁጥሩን በመቀነስ ማዳከም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በአጠቃላይ ቅድሚያ የተሰጠው መንጋውን የማስወገድ ሥራ በመሆኑ በሰብል ላይ ያደረሰውን ጉዳት በውል ማወቅ እንደማይቻልም ጠቅሰዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 27/2012
ኢያሱ መሰለ