አዲስ አበባ፡- የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን በሥራ ዕድል ፈጠራ ዙሪያ የተለያየ ተግባር ያላቸውን ተቋማት አቀናጅቶ በመምራት፣ በዘርፉም ጠንካራ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት እንዲኖር፣ በአጠቃላይ የመንግሥት የሥራ ዕድል ፈጠራ አጀንዳን የሚመራ መሆኑ ተገለፀ፡፡
የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽነር ዶክተር ኤፍሬም ተክሌ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ ኮሚሽኑ ከአንድ ዓመት በፊት የተቋቋመ ሲሆን፣ ተጠሪነቱም ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ነው፡፡ ዋና ተግባሩም በዘርፉ ላይ የሚንቀሳቀሱትን በማስተባበር፣ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ የሚጎለብትበትን በማመቻቸት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራ ከየት ወዴት እየሄደ እንደሆነና እንደመንግሥት መከናወን ያለባቸውን ተግባራት መከታተል፣ ጠንካራ የሆነ የመረጃ አያያዝ እንዲኖር በማድረግ በአጠቃላይ የሥራ ዕድል ፈጠራ አጀንዳን መምራት ነው፡፡
አዳዲስ ንግዶችን ለማስፋፋት፣ ጥራቱን የጠበቀና የተሻለ የቅጥርና የግል ሥራ ለመፍጠር፣ ገበያውን ማዕከል ያደረገ ክህሎት ያለው ሥራ ፈላጊን የሚያገናኝ ሥርዓት ለመዘርጋት በአጠቃላይ በሥራ ዕድል ፈጠራ ውጤታማ ለመሆን አመቺ የፖሊሲ ምህዳር ያስፈልጋል ያሉት ዶክተር ኤፍሬም የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትኩረት ያደረገ የመንግሥት፣ ከመንግሥት ውጪ የሚገኝ ሀብትንና ሌሎችንም ለማሳለጥ የሚያስችል የሥራ ምህዳሩን የሚያሰፋ የመንግሥት ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
ለብዙ ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠርና በማስተባበር ተግባራቸውን ሲወጡ የነበሩ የከተማ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ፣ ሌሎችም የዘርፉ ተቋማትን በማስተባበር እንዲሁም የፌዴራልና የክልል መንግሥታት በአንድ እቅድ እየተመሩ በመስራት ውጤታማ እንዲሆኑ በፖሊሲ ተደግፎ ማስተባበር ሲቻል እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በሥራ ዕድል ፈጠራ በተሟላና ተአማኒነት ያለው መረጃ በማቅረብ በኩልም ክፍተት እንደነበር የጠቆሙት ዶክተር ኤፍሬም፣ ጠንካራ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት እንደሚዘረጋም አመልክተዋል፡፡
የሀገሪቱ ኢኮኖሚ አሁን ባለው ከቀጠለ እኤአ እስከ 2025 ለ16 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅም መኖሩን አመልክተዋል፡፡ የሥራ ዕድል ዕቅዱ ግብርና፣ አምራች ኢንዱስትሪና ሌሎችንም መሠረት ያደረገ ቢሆንም ግብርና ሰፊውን ድርሻ እንደሚወስድ ጠቁመዋል፡፡ የሥራ ዕድሉ ወጣቶችና ሴቶችን ማዕከል ያደረገ ቢሆንም በተለይ የሴቶችን የኑሮ፣የትምህርትና ክህሎት ግምት ውስጥ ባስገባ ቅድሚያ እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡
ዘአዘዲስ ዘመን ጥቅምት 27/2012
ለምለም መንግሥቱ