አዲስ አበባ፡- የመደመር እሳቤ የኢትዮጵ ያውያንን ውስጣዊ አንድነት የሚያጠናክር መሆኑን የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ተናገሩ፡፡
በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተጻፈው “መደመር” መጽሃፍ ትናንት አዲስ አበባ ለሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላትና አጋር ድርጅቶች በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አዳራሽ ማብራሪያ በተሰጠበት ወቅት አስተያየታቸውን የሰጡት ዲፕሎማቶች መጽሐፉ የኢትዮጵያን ችግሮች በአገር በቀል እሳቤ መፍትሄ ለመፈለግ ታስቦ የተዘጋጀ በመሆኑ አንድነትን በማጠናከር ወደ ዕድገት የሚደረግን ጉዞ እንደሚያፋጥን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ራፋይል ሞራቭ እሳቤው ብልጽግናን ዓላማ ከማድረጉም ባሻገር አሳታፊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸው፤ ለኢትዮጵያውያን የውስጥ ችግሮች ትክክለኛ አገር በቀል መፍትሄ ያስቀመጠ መሆኑን ጠቁመዋል።
መደመር ግላዊ ፍላጎቶችን በማስወገድ የጋራ ጥቅምን የሚያስቀድም እሳቤ በመሆኑ በመቻቻልና አብሮ በመስራት ወደ ብልጽግና ለመሸጋገር ሚናው ላቅ ያለ ነው ያሉት አምባሳደሩ፤ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር የሚያግዛት መሆኑንም አስረድተዋል።
የዓለም አቀፉ የእንስሳት ምርምር ተቋም አስተዳደር ሃላፊ ሚስ ጋሊ አሚር የመደመር እሳቤ በአንድነትና አገራዊ ስሜት ወደ ዕድገት ጎዳና የሚደረግን ጉዞ አመላካች ነው ያሉ ሲሆን፤ በተለይም የግብርናውን ዘርፍ ለማሻሻል ያስቀመጣቸው የመፍትሄ ሃሳቦች የሚበረታቱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የዓለም የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ መሆናቸው በቀጠናው ሰላምን ለማምጣት ያደረጉት ጥረት ዓለም አቀፋዊ እውቅና ማግኘቱን ያሳያል ያሉት ሃላፊዋ፤ ይህንን ልምዳቸውን ለሌሎች ለማካፈል መጽሃፉ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው አብራርተዋል።
እሳቤው እርስ በእርስ በመነጋገርና በመግባባት ችግሮችን የመፍታት እንዲሁም የጋራ ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ጉዳይን በግልጽ ስለሚያሳይ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም ህዝቦች ጠቃሚ እንደሆነም ሚስ ጋሊ ተናግረዋል።
በዚህ የመጽሀፍ እሳቤ እንደ አፍሪካዊ ኩራት የተሰማቸው መሆኑን የገለፁት የምእራብ ሰሀራ ሪፐብሊክ ዲፕሎማት መሀመድ ሀማዲ፤ ‹‹በአሁኑ ወቅት አህጉሪቱ የዓለምን ትኩረት እየሳበች በመሆኑ አፍሪካውያን አንድነታችንን በማጠናከር እድገታችን እንዲፋጠን የመደመር እሳቤ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው›› ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሁለንተናዊ እድገትና ሰላም መጠበቅ እየተጫወተች ያለውን ሚና ይበልጥ የሚያጠናክር ነው ያሉት ሚስተር መሀመድ፤ እሳቤው ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ሀገራት በምሳሌነት የሚጠቀስ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራትና ከአፍሪካ እንዲሁም ከዓለም ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር በውጭ የሚኖሩ ዜጎቿ የእድገቱ አካል እንዲሆኑ መጽሀፉ በውጪ ግንኙነት እይታው ያሰፈረው ሃሳብ ጠቃሚና የሚደነቅ መሆኑንም ሚስተር መሀመድ ጨምረው ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 26/2012
በድልነሳ ምንውየለት