አዲስ አበባ፡- ‹‹ ትምህርት ቤቱ ትውልድ ገንቢ ወይስ አምካኝ?›› በሚል ርዕስ የግሪክ ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤትን አስመልክቶ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ነሐሴ አንድ ቀን 2011 ዓ.ም በተሠራው ዘገባ ትምህርት ሚኒስቴር መፍትሔ እንደሚሰጥ ቃል ቢገባም ‹‹ጉዳዩ ከእኔ በላይ ነው›› በሚል እርምጃ እንዳልወሰደ አስታወቀ፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ኢንስፔክሽን ዳይሬክተር አቶ አስፋው መኮንን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ትምህርት ቤቱ በኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት ሥም ተከፍቶ የግሪክን ማህበረሰብ እያስተማረ ባለመሆኑ፣ ለመንግሥትም ግብር ገቢ ስለማያስገባ እንዲሁም ከወሲባዊ ትንኮሳ ጋር ተያይዞ ቅሬታ ስለቀረበበት ወደ ኢንቨስትመንት ይቀየራል ተብሎ ነበር። ይሁን እንጂ በይፋ ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤቱ ራሱን ባለመዝጋቱ በጉዳዩ ላይ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር መምከር አስፈልጓል።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጣልቃ መግባት ስላለበት መረጃው መሰጠቱንና በትምህርት ቤቱ ላይ የሚነሳው ጉዳይ በአገራት መካከል ካለ ግንኙነት ጋር ስለሚገናኝ ረጋ ተብሎ መታየት አለበት በሚል አቋም መያዙን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
ዳይሬክተሩ ትምህርት ቤቱ መንግሥት ወደ ኢንቨስትመንት እንዲገቡ አቅጣጫና ሕግ ካስቀመጠላቸው ለመፈፀም ፈቃደኛ እንደሆነ ቀና ምላሽ መስጠቱን በማንሳት፤ ከሕገወጥ ዕፅ ዝውውር ጋር ተያይዞ ሲነሱ በነበሩ ቅሬታዎች ላይ ማስረጃዎችን አጠናቅሮ በድርጊቱ ተሳታፊ በሆኑ ተማሪዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን፤ አጠቃላይ እልባት ለመስጠት ጊዜ የሚጠይቅና የመንግሥትን ጣልቃ ገብነት የሚፈልግ መሆኑን አስረድተዋል።
ዳይሬክተሩ በተያዘው በጀት ዓመት በ1987 ዓ.ም የግልና ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤቶችን አስመልክቶ የወጣው አዋጅ ማሻሻያ እንደሚደረግበት ገልፀው፤ የሕግ ማስተካከያው በግሪክ ኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤትና በሌሎችም ሲነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን እንደሚያቃልል አመላክተዋል።
የወላጅ ኮሚቴ በአዲስ መልክ እንደተቋቋመና ትምህርት ቤቱ በጋራ መሥራት እንዳለበት ከስምምነት መደረሱን በመግለጽ፤ አጠቃላይ ቅሬታዎቹን ለመቅረፍ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ቢሆንም ጉዳዩ እስከመቼ እልባት ያገኛል? የሚለውን ግን እንደማይታወቅ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
ግሪክ ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት ‹‹ዜጎች በአገራቸው መማርም ሆነ መሥራት እንዳይችሉ በሚያደርግ ትምህርት አሰጣጥና በግብረሰዶም ተግባር ላይ ተሰማርቶ ትውልድ እያመከነ ነው›› በሚል ቅሬታ እንደቀረበበት ይታወሳል። በግለሰቦች የቀረበውን ቅሬታና አራት የተለያየ ማህተሞች የመጠቀሙን እንቆቅልሽ በተመለከተ የትምህርት ቤቱ አስተዳደር ያስተባበለ ሲሆን፤ ትምህርት ሚኒስቴር ግን በትምህርት ቤቱ ተገኝቶ እንዳረጋገጠና የቅሬታውን ተገቢነት አምኖ መፍትሄ እንደሚሰጥ ገልፆ እንደነበር ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 26/2012
ፍዮሪ ተወልደ