አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ ለተፈጠረው አለመረጋጋትና የሠላም መደፍረስ የብዙሃን መገናኛ በቀጥታ ምክንያት ባይሆኑም ጉዳዩን በማራገብ አባብሰውታ የሚሉ አልታጡም፡፡ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም ችግሩ እንዲፈታ እንዳልሰሩም ይገለጻል፡፡ ‹‹ችግሩ በአንድ ጀንበር የተፈጠረ ሳይሆን፤ በየዕለቱ ከሚተላለፉ ቅስቀሳዎች ተከማችቶ ዛሬ ላይ እየተወራረደ ነው፣ ብዙሃን መገናኛ ትውልድ ማንቂያ፣ መረጃ ማስተላለፊያና ማስተማሪያ የመሆናቸውን ያክል ባግባቡ ጥቅም ላይ ካልዋሉ ለእርስ በእርስ ግጭት የሚዳርጉ ይሆናሉ›› የሚል አስተያየት ይደመጣል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ፤ ከለውጡ ትሩፋቶች የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት አንዱ መሆኑ ተጠቁሟል። አንዳንድ መገናኛ ብዙሃንና የማህበረሰብ አንቂዎች ነጻነትን ሽፋን በማድረግ ህዝብን ከህዝብ ጋር የሚያጋጩ መረጃዎችን እያሰራጩ እንደሚገኙ ያስረዳሉ። የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን አስፈላጊውን የእርምት እርምጃ እንዲወስድም አሳስበው ነበር።
የአሀዱ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥበቡ በለጠ፤ በአንድ አገር የሚገኝ ብዙሃን መገናኛ የአገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታ እንደሚመስልና የፖለቲካ ሥርዓቱም ይህንኑ ተከትሎ የተዘረጋ መሆኑን ይናገራሉ።
ሚዲያው ችግር ውስጥ የገባውም የአገሪቱን የፖለቲካ ቅርጽ ይዞ መሆኑን በማመልክት፤ ሚዲያውንና የፖለቲካ ሥርዓቱን መለየት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።
ብዙሃን መገናኛ ገለልተኛ ሆነው መዘገብና በማንነት ላይ መሰረት አድርገው ከሚቀርቡ ትርክቶች መጠበቅ አለባቸው ፤ በሌሎች ላይ የስነ ልቦና ጫና በማድረስ ሌላ ጉዳት እንዳያስከትሉ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው ያስረዳሉ።
‹‹ተደጋጋሚ ትርክቶች የወጣቱን አእምሮ ለበቀል እንዳያነሳሱ ከድርጊቱ መቆጠብ ይገባል፤ ማንነት ላይ የተመሰረቱ ትርክቶችም ከዓመታት በኋላ ተጽዕኖ ሊፈጥሩ የሚችሉ ናቸው፤ እነዚህ ሁሉ የሚታዩት ችግሮች በሚዲያ የተሰሩ ናቸው›› ይላሉ።
ከለውጡ በፊት በርካታ ሚዲያዎች ተሰድደው ከውጭ አገር ሲሰብኩ መቆየታቸውን የሚናገሩት አቶ ጥበቡ፤ አሁን ደግሞ በተሰጣቸው ነጻነት አገር ውስጥ ገብተው ሚዲያውን በመጠቀም ብሄር ተኮር በመሆን ህዝብን ሲያነሳሱ እንዳስተዋሉና ተግባሩ ትክክል ባለመሆኑ በሃላፊነት ስሜት መስራት እንደሚያስፈልግም ይመክራሉ።
ባለሙያውን በየጊዜው በስልጠና ማገዝ፣ ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግና የባለሙያዎችን ተሳትፎም ማሳደግ እንደሚገባም ይጠቁማሉ። አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ህዝብን በመቀስቀስ የብሄር ግጭቶች እንዲቀሰቀሱ በማድረግ ለብዙ ስህተቶች የሚዳርጉ ሚዲያዎች ከድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባ ያሳስባሉ።
የሚዲያ አሰራርን ከፖለቲካ ፓርቲ አባሎችና አክቲቪስቶች እጅ አውጥቶ ነጻ ሆነው ለሚሰሩ ባለሙያዎች መስጠት፣ጋዜጠኝነትና አክቲቪዝምን መለየት፣ የሚዲያ ካውንስልን በማጠናከር ዘገባዎችን እየገመገመ ሪፖርት እንዲያቀርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ፣ አዲሱን የመገናኛ ብዙሃን ረቂቅ አዋጅ ፈጥኖ በማጸደቅ ወደ ትግበራ በማስገባት የሚዲያ አሰራርን ማጎልበትና ሚዲያን ከመንግስት ጫና በማላቀቅ ነጻ ማድረግ እንደሚገባ ይጠቁማሉ።
የማህበራዊ ድረ ገጽ ተጽዕኖ ቀላል አይደለም የሚሉት አቶ ጥበቡ፤ መንግስት መረጃ ፈጥኖ እንደማይሰጥ ይናገራሉ። በመሆኑም በተለያየ ማህበራዊ ሚዲያዎች ትርጓሜ የሚሰጥበት ሁኔታ ለግጭት እንዳይዳርግ መንግስት በትክክለኛ መንገድ መግለጫ መስጠት፣ ጋዜጠኞችም ችግር አለበት በተባሉ ቦታዎች በነጻነት ሊዘግቡ የሚችሉበት ሁኔታ ማመቻቸት መልካም መሆኑን ያመለክታሉ።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ ፤ ፖለቲካው ላይ ያለው ሽኩቻና ትኩሳት ሚዲያው ላይ መንጸባረቁን ፤ በብዙሃን መገናኛ ቅጥ ያጣ ወገንተኝነት ጎልቶ መውጣቱን፣ የፖለቲካው ሽኩቻ ወደ ሚዲያ መዞሩና ሚዲያውም ይህንን መፍቀዱ ተገቢ አለመሆኑን ፤ የተለያዩ ፍላጎቶች በሚዲያው መንጸባረቃቸው አካሄዱን እንዳከበደው ይናገራሉ።
ሚዲያው የተሻለ ነጻነት አግኝቶ እንዲሰራ መንግስት ያስቀመጠው አቅጣጫ እንደነበረ ያስታወሱት ዶክተር ጌታቸው፤ ባለስልጣኑ ሚዲያዎቹ ነጻነታቸውን ተከትለው በሃላፊነት ይሰራሉ ብሎ በማመን ነጻ አድርጓቸው እንደነበር በማስታወስ፤ በሂደት ሙያን መሰረት ያደረገ ሥራ እየቀረ ሌላ መንገድ በመምረጥ ሂደቱን ያበላሹ መኖራቸውን ይጠቁማሉ።
እንደ ዶክተር ጌታቸው ማብራሪያ፤ በሽግግር ጊዜ ብዙሃን መገናኛ ሳይወግኑ ሽግግሩን መደገፍ ይጠበቅባቸዋል። በህብረተሰብ ፍላጎት የመጣ ለውጥ በመሆኑ፣ ህብረተሰብን የሚያገለግሉ በመሆናቸው ሚዛናዊ ውይይት እንዲደረግ መፍቀድ ይጠበቅባቸዋል። ግጭትን ከመቀስቀስ ርቀው ሃሳቦች በነጻነት እንዲንሸራሸሩ መፍቀድ ይኖርባቸዋል። አንዱን ሃሳብ ማጉላት፣ ሌላውን ደግሞ መጨቆን ተገቢነት የሌለው ተግባር ነው።
ሙያው የሚፈቅደው የስነ ምግባር መርሆዎችን ማክበር ይገባቸዋል ፣ ግጭትን የሚቀሰቅስ ሃሳብ መተላለፍ አይገባም፣ ብሄርን በብሄር ላይ የሚያነሳሳ ሃሳብ መተላለፍ አይኖርበትም ፣ ባለሙያዎቹና ባለቤቶቹ ሃላፊነት የሚሰማቸው መሆን አለባቸው እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ።
‹‹በሚዲያ ላይ የእከሌ ብሄረሰብ ሰዎች ሽንኩርት የምትከትፉበትን ቢላዋ ይዛችሁ ተደራጁ የሚል ቅስቀሳ ማድረግ የተደፈረበት ጊዜ ነው። ይህ አላዋቂነት ብቻ ሳይሆን ሃላፊነት የጎደለው ነው›› የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ ባለሙያዎቹ ተጠሪነታቸው ለህዝብ፣ ለአገርና ለህገ መንግስት ብቻ ሳይሆን፤ ለህሊናቸውም ጭምር መስራት እንደሚጠበቅባቸው ያስረዳሉ።
ዳይሬክተሩ ‹‹ጋዜጠኞች ራሳቸውን እያዩ እንዲያስተካክሉ ግብረ መልስ እየሰጠን እንገኛለን። የብዙሃን መገናኛ ሲከፈቱ የህብረተሰብ ድምጽ ይሆናሉ በሚል እሳቤ በመሆኑ በስሜት ተነስቶ መዝጋት አይቻልም። ለማረም ይበጃል የሚባሉ አማራጮችን እንወስዳለን። ከዚህ ባለፈ ግን ከግብረ መልስ አልፈን ማስጠንቀቂያ እንጽፋለን። በማስጠንቀቂያው መሰረት የማይታረሙ ከሆነ በብሮድካስቱ የተቀመጡ ሌሎች ርምጃዎችን በሂደት እንወስዳለን›› ብለዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 26/2012
ዘላለም ግዛው