ኢዜአ፦ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በህዳሴው ግድብ ላይ ያላቸውን የሃሳብ ልዩነት በውይይት ለመፍታት የጀመሩትን ሥራ እንደሚደግፉ ገለጹ። ውይይቱ አገራቱ በግድቡ ዙሪያ ያላቸውን አቋም የሚገልጹበት እንጂ የቴክኒክ ጉዳዮች አጀንዳ እንዳልሆነ ተጠቁሟል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ይህን ያሉት ትናንት ከግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱል ፋታህ አል ሲሲ ጋር በስልክ በተወያዩበት ወቅት ሲሆን፤ ሦስቱ ሀገራት በውይይት ላይ የተመሰረተ ስምምነት እንዲፈጥሩ ለሚያደርጉት ድጋፎች ትራምፕን ማመስገናቸውን አል ጀዚራ በዘገባው አትቷል።
ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን በአሜሪካ ጋባዥነት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ለመወያየት ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከትናንት በስቲያ ወደ ዋሺንግተን ዲሲ ማምራታቸውን የገለጹት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው አሜሪካ ሶስቱም ሀገራት በግድቡ ዙሪያ ያላቸውን አቋም ለመስማት መጥራቷን ገልጸዋል።
አቶ ነብያት በግብጽ መገናኛ ብዙሃን “ድርድር ነው እየቀረበ ያለው በሚል የሚቀርበው ዘገባ ስህተት” እንደሆነ ጠቅሰው፤ የዋሺንግተን ዲሲው ውይይት ሀገራቱ በግድቡ ዙሪያ ያላቸውን አቋም የሚገልጹበት መሆኑን አብራርተዋል።
የአሜሪካ የገንዘብ ተቋም ኃላፊ ስቴቨን ሙንቺን ጥሪ ያደረጉት ለሶስቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ብቻ እንደሆነና የቴክኒክ ጉዳዮች የውይይቱ አጀንዳ እንዳልሆነም አቶ ነብያት አመልክተዋል።
አቶ ነብያት ኢትዮጵያ በውይይቱ ላይ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያላትን አቋም እንደምታቀርብና የተቋረጠው የሀገራቱ የቴክኒክ ኮሚቴ ስብሰባ እንዲቀጥል በተደጋጋሚ እያንጸባረቀች ያለውን አቋሟን ለአሜሪካ እንደምትገልጽ አመልክተዋል።
የዋሺንግተን ዲሲው ውይይት ኢትዮጵያ ለአሜሪካ በግድቡ ዙሪያ ያላትን አቋም ለማስረዳት መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥርላትና “አሜሪካ የህዳሴ ግድቡ ጉዳይ በቴክኒክ ኮሚቴው ስብሰባ ምላሽ እንዲያገኝ ብታበረታታ የኢትዮጵያ ፍላጎት ነው” ሲሉም አቶ ነቢያት ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 26/2012