l የመድን እና የአነስተኛ ፋይናንስ ስራ አዋጆችም ፀድቀዋል
አዲስ አበባ፡– የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው አምስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ ሦስተኛ መደበኛ ስብሰባው በኢትዮጵያ መንግሥትና በተለያዩ መንግሥታትና ዓለም አቀፍ ተቋማት መካከል የተደረጉና ለልማት ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚውሉ ሰባት የብድር ስምምነት አዋጆችን አፅድቋል፡፡
የብድር ስምምነቶቹ የመንገድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የቆላማ አካባቢ ነዋሪዎች ኑሮ ማሻሻያ፣ የከርሰ ምድር ውሃ መስኖና የገጠር ግብርና ልማት እንዲሁም የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክቶችን ለማስፈፀም የሚውሉ ሲሆኑ፤ ከአምስት እስከ 15 ዓመታት ድረስ የሚቆይ የችሮታ ጊዜ ያላቸው፤ እንዲሁም ከ19 እስከ 40 ዓመታት ድረስ ተከፍለው የሚያልቁ ናቸው፡፡
ምክር ቤቱ ያፀደቃቸው የብድር ስምምነቶች ከ980 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያስገኙ ሲሆኑ፤ አነስተኛ ወለድ የሚከፈልባቸው፣ የወጪ ጫናቸው ያልበዛና ከአገሪቱ የብድር አስተዳደር ስትራቴጂ ጋር የሚጣጣሙ እንደሆኑም ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆኑ የውጭ አገራት ዜጎች በመድንና በአነስተኛ ፋይናንስ ስራዎች ላይ እንዲሳተፉ የሚያስችሉት አዋጆችም ጸድቀዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ምክር ቤቱ ወይዘሮ የሺእመቤት ነጋሽ የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ፤ እንዲሁም ዶክተር ተመስገን ባይሳ የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እንዲሆኑ የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብም በሙሉ ድምፅ አፅድቋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 26/2012
አንተነህ ቸሬ