አዲስ አበባ፦ ለቱሪዝም፣ ለማዕድን፣ ለግብርናና ለኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ቅድሚያ በመስጠት በ 2022 ዓ.ም ከ10 ሚሊዮን ለሚበልጡ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር እየተሰራ እንደሚገኝ የሥራ ፈጠራ ኮሚሽን ገለጸ።
ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የሆነውና የሥራ ዕድልን ለማመቻቸት የተቋቋመው የሥራ ፈጠራ ኮሚሽን ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ይፋ ያደረጉትን ፕሮጀክት ለመጀመሪያ አምስት ዓመት ለመተግበር 300 ሚሊዮን ዶላር መመደቡን አስታውቋል።
ለቱሪዝም፣ ለማዕድን፣ ለግብርናና ለኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፎች ቅድሚያ በመስጠት የሚተገበረው ፕሮጀክት የኢኮኖሚ እድገትን ለማስገኘት ብርቱ አቅም ያለው መሆኑ ታምኖበት እንደሆነ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን የመደበው ገንዘብ በተለይ በሥራ ፈጠራ ላይ የተሰማሩ ወጣቶች፣ አነስተኛና መካከለኛ የንግድ ተቋማት ፈጠራ በታከለበት መልኩ የተሻለ ምርታማነትን እንዲያስመዘግቡ በማገዝ ላይ ያተኩራል።
ኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ የተሻለ እንቅስቃሴ ያሳይ ዘንድ ፖሊሲና ደንቦችን ለማሻሻል እያደረገች የምትገኘው እንቅስቃሴ እንዲሁም የስራ ዕድል ፈጠራ ለበርካታ ዓመታት በመንግስት የልማት ግቦች ውስጥ ድርሻ ይዞ እየተሰራበት መቆየቱ በማስተር ካርድ እንድትመረጥ አስተዋጽዖ ማበርከቱን ኮሚሽኑ ለዝግጅት ክፍላችን የላከው መግለጫ ያትታል።
በዘርፉም ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ተቀርጸው መጠነ ሰፊ ስራዎች ሲከናወኑ ቢቆዩም ኢኮኖሚው በማደጉ የስራ ገበያው ከሰራተኛ ቁጥር ጋር ሊመጣጠን እንዳልቻለም ነው ያመለከተው። የግሉ ዘርፍም ሚና በሚፈለገው ደረጃ አለማደጉ የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትና የስራ ዕድል በበቂ ሁኔታ ማረጋገጥ እንዳልተቻለ ነው የተብራራው።
መንግስት በዘርፉ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማስቀጠል፣ ሰላምና መረጋጋትን በማስፈን የዜጎችን የስራ ዕድልን ማረጋገጥ ወሳኝ ተግባሩ መሆኑን በመገንዘብ እየሰራ እንደሚገኝም መግለጫው አስቀምጧል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 26/2012
ዘላለም ግዛው