አዲስ አበባ፡- የግንባታ ሥራው 83 በመቶ የደረሰው የበለስ 1 ስኳር ፋብሪካ በመጪው ሚያዝያ ወር የሙከራ ምርት እንደሚጀምር ስኳር ኮርፖሬሽን አስታወቀ። የኦሞ አንድ ስኳር ፋብሪካ ቀሪ የግንባታ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ከቻይና ኩባንያ ጋር ስምምነት ሊደረግ መሆኑም ተገልጿል፡፡
በኮርፖሬሽኑ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን የሚዲያ ቡድን መሪ አቶ አሰግድ ተስፋዬ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በመንግስት ውሳኔ ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የተወሰደውና የግንባታ ሥራው “ካምስ” እየተባለ ለሚጠራ የቻይና ኩባንያ የተሰጠው የበለስ 1 ስኳር ፋብሪካ በአሁኑ ወቅት ሥራው 83 በመቶ እየተጠናቀቀ በመሆኑ በመጪው ሚያዝያ ወር የሙከራ ምርት ይጀምራል፡፡
እንደ ቡድን መሪው ገለጻ የበለስ ስኳር ፋብሪካ ተገንብቶ ያለመጠናቀቁ እንጂ የሸንኮራ ልማቱም ከፋብሪካው ግንባታ ጋር በተጓዳኝ በተጣጣመ መልኩ እየተሰራ ይገኛል፡፡
አቶ አሰግድ የኦሞ 1 ስኳር ፋብሪካን ግንባታ ለማጠናቀቅ በመንግስት ውሳኔ ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ላይ በመውሰድ ቀሪ ስራዎቹን ለማጠናቀቅ “ጂጂአይሲ” ከሚባል የቻይና ኩባንያ ጋር የዋጋ ድርድር በማድረግ ወደ ስራ ለመግባት ዝግጅት እየተደረገ ሲሆን፤ የኮርፖሬሽኑ ቦርድ ውሳኔ እንዳሳለፈ ሥራው እንደሚጀመር ተናግረዋል።
አቶ አሰግድ የኦሞ 2 ና 3 የስኳር ፋብሪካዎች የሙከራ ምርት ያካሄዱ ሲሆን፤ የፋብሪካውን ቀሪ ሥራዎች በማጠናቀቅ በምርት ሂደት የታዩ ጉድለቶችን እስከ ታህሳስ ወር በማሟላት ፋብሪካዎቹ በሙሉ አቅማቸው ወደ ምርት እንዲገቡ ዕቅድ መያዙን ፤ የወልቃይት ስኳር ፋብሪካ ግንባታም በመፋጠን ላይ መሆኑን አስረድተዋል።
ስኳር ኮርፖሬሽን በ2012 በጀት ዓመት በስምንት ፋብሪካዎች አራት ነጥብ 836 ሚሊዮን ኩንታል ለማምረት ማቀዱ ተገልጿል። ኮርፖሬሽኑ በአንደኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን አቅድ 11 ፋብሪካዎችን በመገንባት የአገር ውስጥ ፍጆታን ከመሸፈን አልፎ ለዓለም ገበያ እንደሚያቀርብ ዕቅድ ቢኖርም ከ10 ዓመት በኋላም የአገር ውስጥ ፍጆታን ማሟላት አልቻለም።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 26/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ