አዲስ አበባ፡- በዘንድሮው በጀት አመት በሰብል ምርት አሰባሰብ ወቅት የምርት ብክነት እንዳይኖር ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ተወካይ ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ደንዳኖ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤በ2011/2012 የምርት ዘመን ከ12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ በሰብል ተሸፍኗል፤ከዚህ ወር ጀምሮ በአብዛኛው ቆላማ በሆኑ የሃገሪቱ ቦታዎች የደረሱ ሰብሎች ይሰበሰባሉ።በስምጥ ሸለቆ፣ ሰሜንና ደቡብ ኢትዮጵያ ባሉ አካባቢዎችም የደረሱ ሰብሎችን መሰብሰብ ተጀምሯል ።
በሰው ጉልበት የሚሰበሰቡ የደረሱ ሰብሎችን አርሶ አደሩ ሳይረግፉ አስቀድሞ መሰብሰብ እንዲችል ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ መሰራቱን ጠቅሰው፣ በአርሶ አደር ጉልበት ከሚሰበሰበው ውጪ በኩታ ገጠም ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች ላይ የሚገኙ ሰብሎች ደግሞ በኮምባይነሮች በመታገዝ ጥራቱን በጠበቀ መልኩ እንዲሰበሰቡ ሰፊ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።
ለዚህም ከአንድ ወር በፊት ከኮምባይነር አቅራቢ ድርጅቶች ጋር የጋራ ግንዛቤ እንዲኖር መደረጉን ተወካይ ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፤ ባለሃብቶችም ያላቸውን መሳሪያዎች ጠግነው ወደስራ እንዲገቡ መንግስት መለዋወጫ እቃዎችን የሚያቀርቡ ድርጅቶችን ያካተተ ውይይት ማካሄዱን ጠቁመዋል።
እንደ ተወካዩ ገለጻ፤በሜካናይዜሽን ግብርና ለሚሰበሰበው ምርትም እስከ 1 ሺ የሚጠጉ ኮምባይነሮች ስራ ላይ እንዲውሉ ይደረጋል። ኮምባይነሮቹ በወጣላቸው ፕሮግራም መሰረት እህል ቀድሞ በደረሰባቸው አካባቢዎች ላይ ምርት እንዲሰበስቡ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል ።
ኮምባይኖሮቹ ሙሉ በሙሉ በምርት አሰባሰቡ ሂደት ላይ እንዲውሉና ምርት እንዳይባክን ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራም ተወካዩ ጠቅሰው፣አርሶ አደሩም ምርቱ ሳይባክን እንዲሰበሰብለት በየአከባቢው ያሉ የግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ እያደረጉለት መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
በዘንድሮ በጀት አመት በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ 406 ሚሊዮን ኩንታል ሰብል ለመሰብሰብ እቅድ መያዙ ይታወቃል።ይህንኑ ምርት ለመሰብሰብ የሚስችሉ ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እንደተከናወኑ ከግብርና ሚኒስቴር የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 25/2012
አስናቀ ፀጋዬ