ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክተው ከትናንት በስቲያ በሰጡት መግለጫ፤በኦሮሚያ ክልል በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ የተጎዳው ሁሉም ነው፤ስለሆነም የህግ የበላይነት በማስፈን ህዝቡ እንዳይጎዳ መንግሥት የሚጠበቅበትን እንደሚተገበር አስታውቀዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን መግለጫ አስመልክቶ አስተያየታቸውን እንዲያጋሩን የጠየቅናቸው የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስተላለፉት መልዕክት ከወትሮው በተለየ መልክ መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስጠበቅ አቋም መያዙን ያመለከተ እንደሆነ ተናግረዋል።
መንግስት እስከዛሬ ድረስ በየቦታው ለህዝቦች መፈናቀልና ሞት ምክንያት የሆኑ ግጭቶችን በሆደ ሰፊነት ማለፉ ተገቢ እንደነበር ጠቅሰው፤የተሰጠውን ሰፊ ምህዳር በአግባቡ ካለመጠቀም የተነሳ በአንዳንድ አካባቢዎች ችግሮች እየበረቱ መምጣታቸውን ተከትሎ አሁን መንግስት የወሰደው አቋም ተገቢና ወቅታዊም ነው ሲሉ ይገልጻሉ።
‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ እዚህም እዛም በድንገት የሚፈነዳውን ግጭት አስቀድሞ ለመተንበይና ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ነው።››ያሉት ፕሮፌሰሩ፣መንግስት የመከላከያ ሰራዊትን ግጭት ወደ ተቀሰቀሰባቸው አካባቢዎች በማሰማራትና ኮማንድ ፓስት በማቋቋም የበኩሉን ጥረት ሲያደርግ መቆየቱንም ያስታውሳሉ። አሁንም የህግ የበላይነትን ለማስከበር የደረሰበት ውሳኔ የሀገሪቱን ሰላም ከማረጋገጥ አንጻር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ይናገራሉ።
አትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ በበኩሉ፤የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ተገቢውን መልዕክት ያስተላለፈ እንደሆነ ጠቅሷል።በተለይም በሰሞኑ ግጭት ህይወታቸው ያለፉ ሰዎችን ከብሄር፣ሐይማኖትና ጾታ አንጻር ያላቸው ስብጥር ሲታይ ግጭት ማንንም ሳይለይ የሚጎዳ መሆኑን መገንዘብ ያስቻለ መሆኑን ተናግሯል።ያለፈው እንዳይደገምም መንግስት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንዳለበትም ነው ያስገነዘበው።
‹‹ሰዎች ኑሯቸውን ለመቀየር ከሚያደርጉት ትግል አልፈው ስለሰላማቸውና ደህንነታቸው መጨነቅ አይገባቸውም፡›› ያለው አትሌቱ፣ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰለጠኑ ሀገራት የሚከተሉትን የዴሞክራሲ መርህ ሲከተሉ መቆየታቸውን ተናግሯል።የሀገሪቱን አውድ ያገናዘበ አካሄድ ቢከተሉ እንደሚሻል ጠቅሶ፣ አሁን የያዙት አቋምም መልካም እንደሆነ አስታውቋል። ህዝቡም ከጎናቸው እንዲቆም ሀሳቡን ጥሪውን አቅርቧል።
የማህበረሰብ ጤና አማካሪው ዶክተር ኤርሲዶ ለንደቦ በበኩላቸው፤ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው የተደረገው ትዕግስት ሀገሪቱን ወደ ከፋ ቀውስ እየከተታት ያለ መሆኑን አስታውቀው፣ከአሁን በኋላ ኮስተር ያለ ህግ የማስከበር ስራ ለመስራት መዘጋጀታቸው ተቀባይነት ያለው እንደሆነም ተናግረዋል።
በቀድሞው ስርዓት መንግስት በህዝብ ላይ ግፍና በደል ያደርግ እንደነበር ያስታወሱት ዶክተር ኤርሲዶ፣‹‹አሁን በተቃራኒው አንዳንድ ግለሰቦች የመንግስትን ህግ እየጣሱ በወገናቸው ላይ ወንጀል ፈጻሚ ሆነዋል።››ይላሉ።መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ወንጀለኞችን ታግሻለሁ ሲል በገለጸው ላይ እንደማይስማሙ ነው ዶክተር ኤርሲዶ የተናገሩት።‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት መግለጫ የሀገሪቱን ሰላም ለማረጋገጥ ተስፋ ሰጪ ነው።››ብለዋል።
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግሬስ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፤የጠቅላይ ሚኒስትሩን መግለጫ በአዎንታዊ ተመልክተው፤‹‹ዋናው የፖለቲካ ችግር ስለሆነ መፍትሄው ችግሩን እንዴት እንፈታ የሚለው ነው።››ይላሉ።‹‹ወደ መደራደርና መነጋገር መሄድ ያስፈልጋል።አለዚያ አገሪቱ ስጋት ውስጥ ትወድቃለች።››ሲሉ ገልጸው፤ለዚህ ደግሞ ወታደራዊ ኃይል ብቻ ፍቱን ነው ማለት እንደማይቻል አመልክተዋል።‹‹መንግስት የህግ የበላይነትን ማስከበር አለበት።ዴሞክራሲያዊ ተቋማትም መንቀሳቀስ አለባቸው።ሁሉም ለሰላሙ የየበኩሉን መወጣት ይጠበቅበታል።››ሲሉም ተናግረዋል።
‹‹መንግስት ትዕግስቱ በዛ የሚሉ አካላት መንግስትን እንዳያሳስቱት ስጋት አለኝ።››የሚሉት ፕሮፌሰሩ፣በወታደራዊ ኃይል ልመራ ማለቱ እምብዛም አዋጭ እንዳልሆነም ነው ያስገነዘቡት።‹‹ሁሉም የየራሱን ሩጫ ለመሮጥ ነው የሚፈልገው እንጂ ለውጡን እንዴት እንምራ የሚለው ላይ አይደለም።ስለዚህ ችግር ፈጣሪውን መለየት ይገባል።››ሲሉም ጠቅሰዋል።
ፕሮፌሰሩ ህዝቡ ለመብቱና ለጥቅሙ የሚሰራውን ለይቶ በማወቅ መከተል እንዳለበት ጠቅሰው፣‹‹የማይፈልገውን ደግሞ ሰላሜን አታጥፋ ማለትም ይኖርበታል።በደፈናው መደገፍ ሳይሆን ለይቶ መከተሉ ተገቢ ነው።››ይላሉ ።‹‹ዝም ብሎ ቲፎዞ መሆን ይጎዳዋልና የትኛውም አካል ትክክል ስለመሆኑ መፈተሽ አለበት።እንዳልጠቀመው ባወቀ ጊዜም መናገር ይኖርበታል።››ሲሉም ያስገነዝባሉ።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 25/2012
ኢያሱ መሰለ