አዲስ አበባ፡- ‹‹በመደመር እሳቤ ኢህአዴግም ሆነ አዲስ የሚመሰርተው ውህድ ፓርቲ ሊመሩበት እንደሚችሉ አስባለሁ›› ሲሉ የቀድሞው የኦነግ መሪ እና የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ ዶክተር ዲማ ነገዎ አስታወቁ።
ዶክተር ዲማ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የመደመር መፅሐፍን ይዘት ተመልክተውታል፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደስልጣን በመጡ በአንድ ዓመት ከመንፈቅ ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ ልትተዳደርበት ትችላለች ብለው ያሰቡትን መጽሀፍ በማዘጋጀታቸው አድናቆቱ አላቸው።
‹‹ኢትዮጵያን የምናስተዳድረው እንዴት ነው? የኢትዮጵያ ችግር ምንድን ነው? ችግሮቹንስ የምንፈታው እንዴት ነው? በማለት ችግሩ ተፈትቶ አገሪቱ ወደ ብልጽግና እንድትሸጋገር ባዘጋጁት በዚህ መጽሀፍ ኢህአዴግም ሆነ አዲስ የሚመሰረተው ውህድ ፓርቲ ሊመራበት ይችላል›› ብለው እንደሚያስቡ አስረድተዋል።
ዶክተር ዲማ፣‹‹መፅሐፉን ምሁራን የሚጎድለው ምንድን ነው?እንደ ሐሳብ ምንድን ነው ያላካተተው? መጨመርስ ያለበት ምንድን ነው? የሚለውን ማየት ይችላሉ። አስተያየት ለመቀበል ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ በሩ ክፍት ነው››ሲሉ ገልጸዋል።
እሳቸውም መጽሀፉ እየተሻሻለ ይሄዳል የሚል ተስፋ እንዳደረባቸው ተናግረዋል። የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ በሐሳቡ ላይ መሰረታዊ የሆኑ ነገሮች መቀመጣቸውን ተናግረው፣ ከሀሳቦቹም በመነሳት የተለያዩ ፕሮግራሞችን ማውጣት እንደሚቻል ገልጸዋል።
በአብዛኛው ነገር ላይም የተመከረበት እና የተስማሙበት እና ያሻግረናል ብለው ያመኑበት መሆኑን ጠቅሰው፣ መመሪያቸው ሊሆን ይችላል የሚል አተያይ እንዳላቸው አስታውቀዋል።
‹‹በርካታ ይዘቶችን ያካተተው ይህ መፅሐፍ ሰዎች ሊተቹት ይችላሉ።››ያሉት ዶክተር ዲማ፣በትችቱም ያነሰውን አሊያም የጎደለውን ሊያሳዩ እንደሚችሉም ጠቁመዋል።በአግባቡ ሳይገመግሙ በመጽሀፉ ላይ ዝም ብሎ ትችት ብቻ ማቅረብ እንደማይጠቅም ጠቅላይ ሚኒስትሩም ተናግረው እንደነበር ጠቅሰው፣እሳቸውም ይህን የጠቅላይ ሚኒስትሩን አባባል እንደሚጋሩት አስታውቀዋል።
‹‹ስለዚህም እኔን ጨምሮ ሁሉም ምሁራን ይህ ሐሳብ ያሻግረናል ወይስ አያሻግረንም የሚለውን ማየት ይገባናል››ሲሉ ዶክተር ዲማ አስገንዝበዋል።
ኢህአዴግ ሲመራበት የቆየው አብዮታዊ ዴሞክራሲ አላሸጋገረንም ሲሉም ተናግረው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ባያሸጋግረንም ደካማ ጎን እንዳለው ሁሉ በጎ ጎንም አለው ሲሉ መግለጻቸውን ጠቅሰዋል።ለእዚህ ምክንያት ያቀረቡትም ያመጣቸው ውጤቶች መኖራቸውን ሲሉ መግለጻቸውንም ተናግረዋል። እነዚህን ውጤቶች ወስደን ስህተቱንም እያረምን በዚያ ላይ ሀገሪቱን እንገንባ ማለታቸውንም አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 25/2012
አስቴር ኤልያስ