አዲስ አበባ፡- የውጭ ሀገር ባለሀብቶች በድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ክፍት በሆኑ ቦታዎች ላይ ሼዶችን በራሳቸው ገንብተው ለማምረት ፍላጎት እያሳዩ መሆናቸውን የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ።
በኢንቨስትመንት ቢሮው የፕሮጀክት ጥናትና ፕሮሞሽን አስተባባሪ አቶ አበራ መንግሥቱ በተለይም ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ኢንዱስትሪ ፓርኩ በ4ሺ 500 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 150 ሺ ሄክታር በሚሆነው ቦታ ላይ 17 ሼዶች በተለያየ መጠን ተገንብተው ባለሀብቶች እየሰሩባቸው ይገኛሉ።
በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ ባለሀብቶች ሼዶችን በራሳቸው ገንብተው ማምረት እንዲችሉ 300 ሺ ሄክታር ባዶ መሬት ክፍት መደረጉንም ጠቅሰው፣ በዚህም መነሻነት የተለያዩ ባለሀብቶች ሼዶችን በመረጡት ዲዛይን በራሳቸው ገንብተው ለማምረት ፍላጎት እያሳዩ መሆናቸውን አስተባባሪው ጠቁመዋል።
በቅርቡም ውሽ የተሰኘ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ በቻይና ሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን (CCECC) ሼድ በማስገንባት ሥራ መጀመሩንም ጠቅሰዋል። ይህንንም ተከትሎ የአሜሪካንና የሌሎች ሀገራት ባለሀብቶች ሼዶችን በራሳቸው ገንብተው ለማምረት ፍላጎት ማሳየታቸውን ተናግረዋል።
ሼዶቹን መገንባት ፍላጎት የሌላቸውና ሼዶቹ የሚያወጡትን ዋጋ ወደ ማሽን መቀየር የሚፈልጉ ካሉም ሼዶች እንዲገነቡላቸው ከተደረገ በኋላ ማሽኖችን በራሳቸው ገጥመው የሼዱን ኪራይ እየከፈሉ እንዲያመርቱ እንደሚደረግም ገልጸዋል።
የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ በኢትዮጵያ ከተገነቡ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በግዙፍነቱ ሦስተኛው መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። በአራት ቢሊዮን ብር ወጪ በኅዳር ወር 2011 ዓ.ም መጨረሻ ግንባታው ተጠናቆ ወደሥራ መግባቱም ይታወሳል። ፓርኩ በሙሉ አቅሙ ማምረት ከጀመረም ከ40 ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርም ተገልጿል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 25/2012
አስናቀ ፀጋዬ