ዛሬ ዛሬ ወጣቱ ለአገር ያለው ፍቅር ጥያቄ ውስጥ ስለመሆኑ በርካቶች ሲናገሩ ይደመጣል። ምሑራን ግን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተመስርቶ ወጣቱ የአገር ፍቅር ስሜት የለውም ከሚል ፍረጃ ይልቅ ወጣቱን ወደጥፋት የሚገፉ ምክንያቶችን ለይቶ መስራት ተገቢ መሆኑን ይገልጻሉ።
ዶክተር ትዕግስት ውሂብ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነልቡና ባለሙያና መምህርት ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ በወጣቶች የአገር ፍቅር ስሜት ዙሪያ ያለው ምልከታ ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር ስለሚያያዝ ምናልባት ወደ ስሜታዊነት የሚያደላና ጠንከር ወዳለ ድምዳሜ የማያደርስ ነው። ምክንያቱም ዛሬ ላይ ባለው ሁኔታ ላይ ተመስርቶ የወጣቱ የአገር ፍቅር ስሜት ተቀዛቅዟል የሚል አካል፤ ከተወሰነ ጊዜ ቀደም ብሎ ቢሆን ምልከታው ሌላ ሊሆን ይችላል።
ለምሳሌ፣ ቀደም ባሉት ጊዜያት ወይም በቀደሙት ስርዓቶች የወጣቱ የአገር ፍቅር ስሜት ከሚነገረው ታሪክና ተረክ አኳያ ጠንካራ እንደነበር ይነገራል፤ አሁን ደግሞ ይህ ተረክ ሲለወጥ ላልቷል ሲባል ይደመጣል። ይህ ደግሞ ትውልዱ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት እየተነገረው የተቀረጸበት የታሪክ ነገራ ውጤት ነው።
ይህ የታሪክ ነገራ ተረክ የሚነገርበት የቋንቋ ክብደት የወጣቱን አገራዊ ስሜት የመሸርሸር ትልቅ አቅም አለው የሚሉት ዶክተር ትዕግስት ተረኩ ጥላቻን፣ በዘር መከፋፈል፣ መገፋፋትና መወጋገዝ በግልጽ የተነገረበትና በተግባር እየታየ የመጣበት ነው። አሁን ላይ ከ20 እስከ 30 ዓመት ያላቸው ወጣቶች በወቅታዊው ችግር ላይ ተሳታፊና የረብሻ አካል ሆኑ ሲባልም ከልጅነታቸው ጀምሮ ሲነገራቸው ያደጉት ይህን መሰል ትርክት የፈጠረባቸው የአገር ስሜት መሸርሸር ውጤት ነው። የቤተሰብ አስተዳደግ፣ የአቻ ተጽዕኖ፣ የትምህርት ቤቶች ቀረጻና የሚውሉበት ቦታ በወጣቱ የአገር ፍቅር መሸርሸር ላይ የየራሳቸው አበርክቶ አላቸው።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነልቡና ትምህርት ክፍል የሶሻል ሳይኮሎጂ ባለሙያና መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ሐብታሙ ወንድሙ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ዛሬ ላይ አገሪቱን እያተራመሱ ያሉት ከ15 እስከ 30 ዓመት እድሜ ያላቸው ወጣቶች መስለው ቢታዩም፤ ከ20 ዓመት በታች ያሉትን በቁጣም ቢሆን መመለስ ይቻላል።
በአንጻሩ ከ40 ዓመት በላይ ያለው ደግሞ ስራም፣ ትዳርም፣ ልጅም ሊኖሩት ስለሚችሉ ከአገር ጋር ያለው ቁርኝት የሚጠነክርበት፣ ለህዝብ ፍቅር የሚያድርበት፣ በግብረ ገብነትም የሚመራበት እድሜ ነው። ከ20 እስከ 40 ዓመት እድሜ ያላቸው ላይ ግን ብዙ መስራት ይገባል።
እንደ ፕሮፌሰር ሐብታሙ ገለፃ በዚህ እድሜ ማመጽና ሕግን መጣስ የተለመደ ነው። በሶሻል ሳይኮሎጂ ሙያ ከ100 ወጣቶች መካከል በአማካይ 12 ልጆች ጥፋት ያጠፋሉ ብሎ ሳይንሱ ያስቀምጣል። ይህ ደግሞ ወጣቶች በቀላሉ የመታለል፣ አርቆ ያለማየት፣ ያለማገናዘብ፣ በፖለቲካው አካባቢ ያሉ ክፋቶችን በአግባቡ ያለመረዳት፣ ወዘተ ምክንያት በሚያደርጉት ተግባር አገርንና ህዝብን ብሎም ንብረትን የማይወዱ ሊመስሉ ይችላል።
ይህ ግን የአገርና ህዝብ ፍቅር ስሜት ሳይኖራቸው ነው ወደሚል ድምዳሜ ላይ የሚያስደርስ ሳይሆን፤ በእድሜ ያካበቱት በቂ ልምድና የማገናዘብ አቅም ባለመገንባታቸው በቀላሉ ስለሚታለሉና ስለሚገፉ መሆኑን መረዳት ይገባል።
ዶክተር ትዕግስት እንደሚሉት፤ በሚታየው ነባራዊ ሁኔታም እየተነገረ ያለው የታሪክ ገጽ ጠንካራ አገራዊ ጥምረትንና ስሜትን በሚገነባ መልኩ ባለመሆኑ፤ በሁሉም አካባቢ አንድ አይነት ባይሆንም አገራዊ ስሜቱ ግልብ እና ከላይ ከላይ የሚታይ እንጂ ጥልቅ አይመስልም።
ይህ ደግሞ እንደየአካባቢው፣ እንደየቤተሰቡ፣ እንደየአደገበት ማህበረሰብ፣ እንደሚሰ ራበት የሥራ ከባቢ፣ እንደሚያገኘው ሰውና ሌሎችም ተጽዕኖ ፈጣሪ ጉዳዮች ይለያያል። የቤተሰብ ተጽዕኖ የዚህ አንድ ማሳያ ሲሆን፤ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ተሸርሽሯል በሚባልበት አካባቢ እንኳን በአስተዳደግና ከቤተሰብ በሚያዩትና በሚያገኙት ነገር ምክንያት ጠንካራ የሚባለው የአገር ፍቅር ይኖራል።
እንደ ፕሮፌሰር ሐብታሙ ገለጻ ደግሞ፤ አሁን በ20ዎቹ እድሜ አካባቢ ያለው ወጣት ታላቅን፣ ፈጣሪን፣ ሽማግሌን፣ ወዘተ የመፍራት ጉዳይን በወጉ አልያዘም፤ በተመሳሳይ የሰብዓዊ መብት የሚሉ ጉዳዮችም በወጉ አልተዋሃዱትም። ይህም ወጣቶቹ ከልጅነታቸው ጀምሮ በእነዚህ እሴቶች ተቃኝተው እንዲያድጉ ያለመሆናቸው ውጤት ሲሆን፤ ቤተሰብ፣ ማህበረሰብና ትምህርት ቤቶችም መስራት በሚገባቸው ልክ ልጆች ላይ አለመስራታቸውን ያሳያል።
ለምሳሌ፣ የተማሪዎችን ሥነምግባር ይቀርጻል ተብሎ የተዘጋጀው ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍል የሚሰጠው የስነዜጋና ስነምግባር ትምህርት በአመዛኙ ተመሳሳይ ይዘት ያለውና ሽምደዳ ላይ ያተኮረ እንጂ፤ ተማሪዎች ከመቻቻል፣ ከውይይት፣ ከፍቅር፣ ከግብረ ገብነትና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ያሉትን ነባራዊ ሁኔታዎች ተረድተውና ድርሻ ወስደው እንዲለማመዱት እድል የሚሰጥ፤ መረጃን ከመስጠት ባለፈም ክህሎትና አመለካከት ግንባታ ላይ ያተኮረ አይደለም።
ዶክተር ትዕግስት እንደሚናገሩት፤ አሁን የአገር ፍቅር የለም ከሚያስብሉ ጉዳዮች መካከል ወጣቱ የአገር ፍቅር ቢኖረው ኖሮ ለምን አንዱ አንዱን ይገድላል፤ ንብረት ያወድማል ወይም ሌላ በአገርና ህዝብ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ተግባራትን ያከናውናል የሚለው ነው።
በእርግጥም በተግባር የማይገለጽ ኢትዮጵያን እወዳለሁ ማለት ለአገርና ወገን ክብርና ፍቅር ከማይሰጥ የማይጨበጥ ቃል የዘለለ አይሆንም። በዚህና መሰል አሁናዊ ጉዳዮች አኳያ ሲታይ ከቀደመው ትውልድ አንጻር ሲታይ አሁን ላይ በሁሉም አካባቢ ነው ባይባልም በተለያዩ ገፊ ምክንያቶች በወጣቱ ላይ የአገር ፍቅር ስሜቱ እየተሸረሸረ መምጣቱን መገንዘብ ይቻላል።
ይህ ደግሞ ትውልዱ በአዎንታዊ እሳቤ ተገንብቶ ማደግ ካልቻለና አገራዊ ስዕል በሌለው ተረክ ውስጥ ማደጉን ከቀጠለ ችግሩ እየከፋ፤ ራስን ባልሆነ የታሪክ ገጽ ውስጥ ማስቀመጥ እየበዛ ይሄዳል። ወደፊት አገር ያስተዳድራል የሚባለውን ከ70 በመቶ በላይ የህብረተሰብ ክፍል የሆነው ወጣትም ያለውን የስነልቡና ተነሳሽነት የበለጠ እንዲወድቅ ያደርጋል። ማህበረሰባዊና አገራዊ ውድቀትንም ያመጣል።
ፕሮፌሰር ሐብታሙ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ በግፊት የሚነዱ ወጣቶች በተበራከቱ ቁጥር አሁን የሚታዩ የጥላቻ ንግግሮች ከንግግር ያለፈ ተግባርን ይጋብዛሉ። የፖለቲከኞች የሽወዳ ጉዞም እየተበራከተ በህዝቦች መካከል ግጭቶችን ያሰፋል። አለፍ ሲልም ያሉት ምልክቶች ከዚህ አለፍ ባለ መልኩ የእርስ በእርስ እልቂት የማይጋብዙበት እድል አይኖርም።
ምሑራኑ እንደሚሉት፤ የአገር ውድቀት ተከስቶ ከመታየቱ ወይም ከመሰማቱ በፊት ቤተሰብ፣ ማህበረሰብና ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ያሉ አካላት ወጣቶች አዎንታዊ አስተሳሰብን አጎልብተውና በአገር ፍቅር ስሜት ታንጸው እንዲያድጉ፤ ለዚህ ድርጊት የማይዳርጋቸውን የአመለካከትና የሞራል ልዕልና እንዲገነቡ ማድረግ ይገባል።
በዚህ ሂደት የሚነግሯቸውና የሚያስተምሯቸው የታሪክ ገጽታዎችም በልካቸው የተቃኙ፤ ስህተቶችን ማረምና መልካም ገጾችን ማጎልበት በሚያስችል አገራዊ ስዕል መሆን ይጠበቅበታል። ከዚህ ባለፈም ሕጎችና ስርዓቶችን እንዲያውቁ ማድረግ፣ ከማሳወቅ ባለፈም ህዝቡ በራሱ የጸጥታ አካላትን ሳይጠብቅ ሕግና ስርዓቶች ማክበርና እንዲከበሩም በራሱ ተነሳሽነት መስራት ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 24/2012
ወንድወሰን ሽመልስ